የአሳድ ከስልጣን መወገድ በኋላ የሶሪያ ክርስቲያኖች ለአገሪቷ ‘ዳግም ውልደት’ እንደሚሆን ያላቸውን ተስፋ ገለጹ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ባለፉት ጥቂት ቀናት ውስጥ ዓማፅያኑ የሶሪያን ትላልቅ ከተሞች በመብረቅ ፍጥነት ሲቆጣጠሩ የዓለም ማህበረሰብ በድንጋጤ ሲመለከት ነበር።
ህዳር 29 ቀን 2017 ዓ.ም. ከወደ ደማስቆ የተሰማው ዜና በእርግጥ ለተቀረው ዓለም ይቅር እና ለሶሪያዉያኑ ራሱ የማይታሰብ ይመስል ነበር። ‘ሃያት ታህሪር አል ሻም’ በተሰኘው እስላማዊ ታጣቂ ቡድን የሚመራው የሶሪያ አማጽያን ጥምረት እሁድ ማለዳ መዲናዋ ደማስቆን በቁጥጥር ስር አውለው የአሳድ ቤተሰብ የ53 ዓመታት አገዛዝን አስወግደዋል።
የአል አሳድ መንግስት መውደቅን ተከትሎ በርካታ ሶሪያዊያን በመዲናዪቱ ጎዳናዎች ወጥተው ደስታቸውን ሲገልጹ የታዩ ሲሆን፥ የመንግስት ወታደሮች ጥለዋቸው በሸሹ ታንኮች ዙሪያ ተሰባስበው ሲጨፍሩ የሚያሳዩ የቪዲዮ ምስሎች ተለቀዋል።
የአሳድ አገዛዝ ብዙውን ጊዜ የአናሳ ሀይማኖቶች ጠበቃ ተደርጎ የሚገለጽ ሲሆን፥ በአሁኑ ጊዜ ድል የቀናው የአማፂው ቡድን በሃገሪቱ ውስጥ አነስተኛ ቁጥር ባላቸው የሃይማኖት ቡድኖች ማለትም እንደ ድሩዞች፣ ኢስማኢሎች፣ ክርስቲያኖች፣ ኩርዶች እና የመሳሰሉት አናሳ ሃይማኖቶች ላይ ያለው አመለካከት ምን እንደሆነ እና እጣ ፋንታቸውስ ምን ይሆናል የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ሆኗል።
የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ግዴታ
የቫቲካን ዜና ብዙ ክርስቲያኖች በአገዛዙ ውድቀት ደስተኛ የሆኑበት ምክንያት ለምን እንደሆነ በአሌፖ የላቲን ሥርዓተ አምልኮን የምትከተል የካቶሊክ ቤተክርስቲያ ቁምስና ካህን የሆኑትን አባ ባጅሃት ካራካችን ጠይቆ በሰጡት ምላሽ “ክርስቲያኖች ‘እንደ ሌሎች ሶሪያውያን ሁሉ’ ለረጅም ዓመታት ምንም ዓይነት ልማት እና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት በሌለበት ጦርነት ውስጥ ስለነበሩ ሙሉ በሙሉ በመዳከማቸው ምክንያት” እንደሆነ ገልጸው፥ “የነበሩበት ሁኔታ ስለመኖር የሚታሰብበት ሳይሆን በህይወት የመትረፍ ጉዳይ ነበር” ሲሉ በአጽንዖት ተናግረዋል።
ፍራንቺስካዊው ካህን እንደተናገሩት አማፂያኑ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ የተወረሱ ንብረቶችን መመለስን ጨምሮ ለክርስቲያኖች ያላቸውን ድጋፍ ያሳዩ እንደነበር ገልጸው፥ አማጽያኑ አሌፖን ተቆጣጥረው ወደ ደቡብ ከተጓዙ በኋላ ክርስቲያኖችን ጨምሮ ለሁሉም አናሳ ቡድኖች “በጣም ጠንካራ የመቻቻል መልዕክቶችን” ሲልኩ ቆይተዋል ብለዋል።
አባ ካራካች በተጨማሪም የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ “አገሪቷን ለማረጋጋት የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ እና ሶሪያውያን የሁሉንም መብቶች የሚያከብር አዲስ ሕገ መንግሥት እንዲያዘጋጁ መርዳት” እንዳለበት አሳስበዋል።
ሶሪያዊው የፍራንቺስካዊያን ካህን ይሄንን አስመልክተው እንደተናገሩት “ይህ እንደሚሆን ተስፋችን ነው፣ ነገር ግን ነገሮች እንዴት እንደሚሆኑ ወደፊት የምናየው ጉዳይ ነው” ብለዋል።
ከአል-ጆላኒ ጋር የነበረው ቆይታ
የቫቲካን ዜና ከካህኑ በተጨማሪም የአሌፖ ሐዋርያዊ ሰበካ ሊቀ ጳጳስ ከሆኑት ከብጹእ አቡነ ሃና ጃሉፍ ጋር ቆይታ አድርጎ የነበረ ሲሆን፥ ሊቀ ጳጳሱ የስልጣን ሽግግሩ ያለ ደም መፋሰስ ስለተከናወነ እግዚአብሔርን አመስግነዋል።
ሊቀ ጳጳሱ “ክርስቲያኖች እና ንብረቶቻቸው እንደማይነኩ እንዲሁም [ታጣቂዎቹ] ሁሉንም ህጋዊ ጥያቄዎቻችንን እንደሚያሟሉ ማረጋገጫ ከሰጣቸው ዋነኛው የአማጽያን ቡድኑ መሪ ከሆነው አል-ጆላኒ ጋር ተገናኝተው እንደተወያዩም ገልጸዋል።
ሊቀ ጳጳስ ጃሉፍ እንዳሉት እስካሁን ድረስ አማጽያኑ ቃላቸውን ጠብቀው ክርስቲያኖችን ‘በታላቅ ጸጋ’ ተቀብለዋል በማለት አብራርተዋል።
ለሃገሪቷ ‘ዳግም ውልደት’ ያለው ተስፋ
የላቲን ሥርዓትን የምትከተለው የደማስቆ ቁምስና ደብር ካህን የሆኑት አባ ፊራስ ሉፍቲ በበኩላቸው የአገዛዙን ውድቀት ሲገልጹ፥ አሁን የመጣው ለውጥ በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዓመታዊ ክብረ በዓል ላይ ያገኙት ስጦታ መሆኑን ገልጸው፥ “ከ53 ዓመታት አምባገነናዊ እና ደም መጣጭ መንግስት አገዛዝ በኋላ የተከሰተ የአዲስቷ ሶሪያ ልደት ነው” ብለዋል።
አባ ሉፍቲ አክለውም የአሳድ መንግስት “ከግማሽ ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎችን ህይወት እንደቀጠፈ ብሎም የሃገሪቷን ኢኮኖሚ ማውደሙን” ጠቁመው፥ በአሁኑ ወቅት ‘የሶሪያን ዳግም ውልደት የምናከብርበት ጊዜ ነው’ ሲሉ አሳስበዋል።
ሆኖም ግን፥ በተለይም በርካታ የውጪ ተዋጊዎችን ጨምሮ አሁን ስልጣን ከያዙት የተለያዩ ታጣቂ ቡድኖች አንፃር የሀገሪቱ የወደፊት እጣ ፈንታን በሚመለከት አስፈላጊ ጥያቄዎችን መጠየቅ እንደሚያስፈልግም አስታውሰዋል።
ካህኑ በመጨረሻም ሶሪያውያን አማፂያኑ ለድል እንዲበቁ በዋናነት ከረዱት ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር በመሆን አገሪቷን ወደ ‘እውነተኛ እና ትክክለኛ ዳግም ውልደት፣ ዲሞክራሲ እና ሰብአዊ መብቶች የሚነግሱባት፣ ከሁሉም ሃይማኖቶች፣ ጎሣዎች እና ቤተ እምነቶች የተውጣጡ ሶርያውያን የሚከበሩበት ሃገር እንድትሆን ጠንክረው መስራት አለባቸው ብለዋል።