ፓትርያርክ ፒዛባላ የጋዛ ክርስቲያኖችን ጎበኙ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ብፁዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒዛባላ ታህሳስ 13 ቀን 2017 ዓ.ም. ወደ ጋዛ ሰርጥ በመጓዝ ከ14 ወራት በላይ የቅዱሳን ቤተሰብ ደብር ቅጥር ግቢ ውስጥ ተጠልለው የሚገኙትን በቁጥር አነስተኛ የሆኑ የክርስቲያን ማህበረሰብን በጎበኙበት ወቅት ለምዕመናኑ ባስተላለፉት መልዕክት “ዓለም ሁሉ ከእናንተ ጋር ነው” ማለታቸው የተገለጸ ሲሆን፥ ብጹዕነታቸው የጋዛ ሰርጥን ለመጎብኘት እሁድ በማለዳ ከኢየሩሳሌም ተነስተው በኤሬትስ መንደር መሻገሪያ በኩል አድርገው ጋዛ እስኪገቡ ድረስ በእስራኤል ወታደሮች እንደታጀቡ ተመላክቷል።
ጉብኝቱን ቢያንስ ለአንድ ቀን ከእሳቸው ጋር የገናን በዓል ለማክበር ተስፋ ባደረጉ ምዕመናን በጉጉት ሲጠበቅ የነበረ ሲሆን፥ ብፁዕ ካርዲናል ፒዛባላ ባለፈው ዓመት ግንቦት 8 ወደ ስፍራው ካደረጉት ጉዞ ቀጥሎ ወደ ጋዛ ሰርጥ ገብተው የቁምስናው ካህን በሆኑት በአባ ገብርኤል ሮማኔሊ የሚመራውን ማህበረሰቡን ሲጎበኙ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ እንደሆነ እና ለደህንነታቸው ሲባል የጉብኝቱ ዜና የተነገረው ማህበረሰቡ ዘንድ ከደረሱ በኋላ እንደሆነ ተገልጿል።
ከጋዛ ክርስቲያኖች ጋር አንድነት
ብፁዕ ካርዲናል ፒዛባላ የቅድመ ገናን እሁድ ነጭ ልብስ በመልበስ እና መስዋዕተ ቅዳሴን በመምራት ከምዕመኑ ጋር በደስታ ያሳለፉ ሲሆን፥ በቅዳሴው ወቅትም ለበርካታ ወጣቶች ቅዱስ ቁርባንን አጋርተዋል።
ፓትርያርኩ በስብከታቸው ወቅት የክርስቲያኑ ማኅበረሰብ የተለያዩ ችግሮችን በጽናት አልፈው እዚህ በመድረሳቸው ያላቸውን አድናቆት በመግለጽ፥ “እናንተ የቤተ ክርስቲያናችን ብርሃን ናችሁ፥ የገና በዓል ደግሞ የብርሃን በዓል ነው፥ በመሆኑም መቼም ቢሆን ሰውን የማይረሳው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም እዚህ ከእናንተ ጋር አለ” ካሉ በኋላ፥ በእነሱ እንደሚኮሩ በመግለጽ፥ “በተለይ ሌላ ለየት ያለ ነገር ስላለ ሳይሆን ከክርስቶስ ጋር ማንነታችሁን ጠብቃችሁ ስለቆያችሁ በእናንተ እንኮራለን” ብለዋቸዋል።
ክርስቲያኖች ብቻ ሳይሆኑ አብዛኛው የዓለሙ ማህበረሰብ ከእነሱ ጋር እንዳለ ያስታወሱት ብጹእነታቸው፥ እናንተም በአርአያነታችሁ የክርስቶስን ብርሃን ለሁሉም ሰው በማምጣት ወደ እናንተ ለሚመለከተው ዓለም አንድ ነገር ልትሰጡ ትችላላችሁ ብለዋቸዋል።
ወደ ቤተልሔም የሚደረግ ጉዞ
ፓትርያርኩ የጋዛን ጉብኝት ካጠናቀቁ በኋላ ማክሰኞ ዕለት ወደ ቤተልሔም በማቅናት ሌላ ስቃይ ውስጥ በሚገኝ ማህበረሰብ አቀባበል ከተደረገላቸው በኋላ የገና በዓል ዋዜማን በቅድስት ካትሪን ቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ ቅዳሴን በማሳረግ እንደሚያከብሩ ይጠበቃል።