ፈልግ

የክርስቶስ ንጉስ ዓመታዊ ክብረ-በዓል መርሃ ግብር በልደታ ማርያም ካቴድራል በድምቀት ተከበረ የክርስቶስ ንጉስ ዓመታዊ ክብረ-በዓል መርሃ ግብር በልደታ ማርያም ካቴድራል በድምቀት ተከበረ 

የክርስቶስ ንጉስ ዓመታዊ ክብረ-በዓል መርሃ ግብር በልደታ ማርያም ካቴድራል በድምቀት ተከበረ

ካቶሊካዊት ቤተ ክርስትያን በታላቅ መንፈሳዊነት ከምታከብራቸው በዓላት አንዱ የክርስቶስ ንጉሥ በዓል ሲሆን፥ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንም ይሄንን ዓመታዊ ክብረ በዓል ህዳር 28 እና 29 ቀን 2017 ዓ.ም. ‘የተስፋው ነጋዲያን ነን’ በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ ሃገረ ስብከት በልደታ ማርያም ካቴድራል በርካታ ገዳማዊያን እና ገዳማዊያት፣ ከተለያዩ ቁምስናዎች የመጡ ምዕመን በተገኙበት በታላቅ ድምቀት አክብራለች።

አዘጋጅ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የክርስቶስ ንጉሥ በዓል እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር በ1925 ዓ.ም. በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፒየስ 11ኛ ‘ክዌስ ፕሪማስ’ (Quas Primas) በተሰኘው ሐዋርያዊ መልእክታቸውን ይፋ ካደርጉ በኋላ የተጀመረ በዓል ነው።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፒየስ 11ኛ በጊዜው ለነበረው ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ መዋቅር መልስ ለመስጠት ይህንን በዓል ያወጁ ሲሆን፥ ጊዜው በታላላቅ አምባገነን ፖለቲካዊ ኃይሎች የተሞላ ከመሆኑ ባሻገር በጊዜው የነበሩት ማህበራዊ መዋቅሮች ለክርስቶስ ቦታ ያልነበራቸው ነበሩ። በርካታ ክርስቲያኖች በፖለቲካው ፈርጣማ ኃይሎች ፍልስፍና በመማረካቸው ክርስቶስ በሕይወታቸው ውስጥ ቦታ እንዳልነበረውና ንጉሣዊ የፍጥረት ጌትነቱንም አይቀበሉም ነበር።

በመሆኑም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፒየስ 11ኛ በጊዜው ለነበሩ ነባራዊ ምልክቶች ትኩረት በመስጠት ይህንን በዓል ሲያውጁ የተወሰኑ ነጥቦችን ግልጽ ለማድረግ አስበው እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ። ከእነዚህም ነጥቦች መካከል ቀዳሚው በሃዋሪያዊ መልዕክታቸው አንቀጽ 32 ላይ እንደጠቀሱት ቤተክርስቲያን ከየትኛውም ፖለቲካዊ ርዕዮተ ዓለም በላይ ነፃነት ያላት በመሆኗ ከመንግስት ተጽዕኖ ነፃ መሆኗን ለማሳየት፣ መሪዎች እና ሕዝቦቻቸው የክርስቶስን ዘላለማዊ ንጉሥነት እንዲገነዘቡ በር ለመክፈት እንዲሁም ክርስቶስ በአማኞች ልብ፣ አዕምሮ፣ አካል እና ሰውነት ውስጥ መንገሥ እንደሚገባው በማሳየት ክርስትያኖች በዓለም ፊት ስለ ክርስቶስ ንጉሥነት ለመመስከር የሚችሉበትን መልካም አጋጣሚ ለመፍጠር እንደሆነ ይታወቃል።

ዛሬም ቢሆን ዓለማችን ከራሷ ምድራዊ መሪዎች ባሻገር ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አትመለከትም። ክርስቲያን መሪዎችም ቢሆኑ መሪነታቸው ከሥልጣን ጋር የተያያዘ የስራ ዘርፍ እንጂ ከክርስቶስ ንግሥና ጋር የሚገናኝ አገልጋይነት መሆኑ አይታያቸውም። ግላዊ ስልጣን፣ የግል ችሎታ እና የግል ሐሳብ ብቻ ሲንሸራሸር እናስተውላለን። ይህ በሁሉም ቦታ የሚታይ ችግር ሲሆን፥ የክርስቶስ ንጉሥ በዓል በዚህ ውስጥ ብቅ ያለው እውነተኛው ንጉሥ እርሱ ብቻ መሆኑን ለመመስከር ነው። ሌሎች ምድራዊ መሪዎች ሁሉ የአንዱ እውነተኛ ንጉሥ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅጥረኞች ናቸው። እውነተኛ አገልግሎታቸውን እና ሥልጣናቸውን የሚያገኙት ከእርሱ ጋር ሠላማዊ ግንኙነት ሲመሰርቱ ብቻ ነው። በጊዜው የነበረው ንጉሥ ጲላጦስ ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ “አንተ ንጉሥ ነህን?” በማለት ጥያቄውን ያቀርባል፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ሲመልስለት “እኔ ንጉሥ እንደ ሆንሁ መናገርህ ትክክል ነው፤ የተወለድሁት፣ ወደዚህም ዓለም የመጣሁት ስለ እውነት ለመመስከር ነው፤ ከእውነት የሆነ ሁሉ ይሰማኛል” በማለት እንደነገረው በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 18፡37 ላይ እናገኛለን።

የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ንጉሥነት ስናከብር ራሱን ለዓለም ቤዛ አድርጎ ያቀረበውን ንጉሥ በዓል እያከበርን መሆኑ ይታወቃል፥ እርሱም በቃሉ እንደሚለው “እንዲሁ የሰው ልጅም ሊያገለግልና ነፍሱን ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም” በማለት ይናገራል።

ይህ ንጉሥ አገልጋይ ሆኖ መጣ፣ ይህ ንጉስ የህዝቡን እግር የሚያጥብ ሆኖ መጣ፣ ይህ ንጉስ እናንተ ሸክም የከበደባችሁ ወደ እኔ ኑ ብሎ መጣ፣ ሰው ወደ እርሱ በመጣ ጊዜ የሚያሳርፍ ሆኖ መጣ። የክርስቶስ ንጉሥነት በትህትና እና በአገልግሎት የተገለጠ ንጉሥነት ነው። በዚህ አይነት ክርስቶስ አዲስ የመሪነት መንፈስ ይዞ ወደ ዓለም መጥቷልና የዓለምን ምድራዊ መሪዎች ገጽታ እና የመሪነት እሳቤ ለውጧል።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትሁት ንጉሥ ነው፥ ይህ ደግሞ ከመጀመሪያው ጀምሮ በተግባር የታየ እውነታ ነው፥ ልደቱ በከብቶች ግርግም ውስጥ እንደነበረ እናስታውሳለን፥ እርሱ ምድራዊውን የንጉሥ ዝና እና ስልጣን ሁሉ ሽሮ በምትኩ አዲስ የንጉሥ መልክ ተክሏል፤ ይህ ንጉሥ ገዢ ሳይሆን አገልጋይ ንጉሥ ነው፥ ሥልጣን ብቻ ሳይሆን ባሳየን ፍቅር በፍቅር እንድንገዛለት ያደርገናል፥ በፍርሀት ሳይሆን በእውነት መንፈስ እንገዛለት ዘንድ ትህትናው ይጠራናል፡፡

ኢየሱስ ንጉሥ ነው! ነገር ግን መንግስቱ ከዚህ ዓለም አይደለም፡፡ የዚህ ዓለም ሰዎች በሀይልና በስልጣን ሌሎችን ይገዛሉ፤ ሌሎችን ከእነርሱ በታች አድርገው ይበዘብዛሉ፣ በኢየሱስ መንግስት ግን ይህ አይነቱ ሥልጣን ቦታ የለውም፥ በዓለም ላይ ኃይል እና ሥልጣን ያላቸው ሁሉ ሥልጣናቸውን በተለያየ መንገድ ይጠቀማሉ ፤ አንዳንድ ጊዜ ይህንን ስልጣን ያለ አግባብ ተጠቅመው ሌሎችን ይበድላሉ፥ ኢየሱስ ግን በመስቀል ላይ ኃይል የሌለው፣ ትሁት ንጉሥ ሆነ፥ “ሌሎችን አዳነ እርሱ በእግዚአብሔር የተመረጠው ክርስቶስ ከሆነ ራሱን ያድን እያሉ አፌዙበት” ፥ ነገር ግን የክርስቶስ መንግስት የትህትና እና የአገልግሎት መንግስት ነው። ኢየሱስ ንጉሥ ነው፣ ነገር ግን መንግስቱ ከዚህ ዓለም አይደለም።

ስለዚህ በዓለም ላይ ያሉ ባለሥልጣናት ሥልጣናቸውን ያለአግባብ በመጠቀማቸው እና በተለያዩ ምክንያቶች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፒየስ 11ኛ “የክርስቶስ ንጉስ በዓል” እንዲከበር ዐወጁ። በመሆኑም የዚህ በዓል መነሻ ባለሥልጣናት ኃይላቸውን ያለአግባብ መጠቀማቸው ነው፤ የኃይል አጠቃቀማቸው ከኢየሱስ የኃይል አጠቃቀም ተቃራኒ ነበር፤ ኢየሱስ ስልጣኑን ያለአግባብ አልተጠቀመም ፤ እርሱ ለባለሥልጣናት የሥልጣን አጠቃቀም አብነት ነው፥ በኢየሱስ መንግስት ለስልጣን መስገብገብ፣ አልጠግብ ባይነት ወይም ግፍ የለም።

በተለያዩ አጋጣሚዎች እንዳየነው የኢየሱስ ሥልጣን ከዚህ ዓለም ባለሥልጣናት ኃይል ጋር ተቃራኒ ነው፥ ኢየሱስ ከቀረጥ ሰብሳቢዎች፣ ከኃጢያተኞች እና ከሴተኛ አዳሪዎች ጋር ሲነጋገር፣ ሲበላ፣ ሲወያይ ይታያል። በዚህም ምክንያት በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 7 ላይ እንደተገለጸው የጊዜው ባለሥልጣናት “በላተኛ እና የወይን ጠጅ ጠጪ፣ የቀራጮችና የኃጢያተኞች ወዳጅ” ብለው ፈረዱበት፥ የዓለም ባለሥልጣናት ክብር ያላቸውን ሰዎች እና ኃብታሞችን ሲቀበሉ፥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ታናናሾችን፣ በማህበረሰቡ ዘንድ የተናቁትን እና ድሆችን ይቀበል ነበር። ዓላማውም ባለሥልጣናት ወደ እነርሱ ከሚመጡ ሰዎች እጅ መንሻ ስጦታ ይፈልጋሉ፤ በአንፃሩ ኢየሱስ ግን ለሰዎች ስጦታ ይሰጥ ነበር፥ ጤና ላጡ ጤናቸውን ይመልሳል፣ ለታሰሩ መፈታትን፣ ለዐይነ ሥውራን ብርሀንን ያድል ነበር።

ኢየሱስ ንጉሥ ነው፤ ንጉሥ ስለሆነ አክሊል ደፍቷል። ነገር ግን የእርሱ አክሊል እንደዚህ ዓለም ባለሥልጣናት አይደለም፥ የእርሱ ዘውድ የእሾህ አክሊል ነው፥ ኢየሱስ ንጉሥ ነውና ባንዲራ አለው፥ የእርሱ ባንዲራ የተቀደሰው መስቀል ነው። ስለዚሀ የእርሱ የሆኑት ሁሉ ይህን ባንዲራ ይዘው እንዲከተሉት በሉቃስ ወንጌል እንደተገለጸው “ሊከተለኝ የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ፣ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ” በማለት ይጋብዛል። ስለዚህ የኢየሱስ መንግስት ከዚህ ዓለም ገዢዎች ተቃራኒ ነው። ኢየሱስ እውነት እና የህይወት ንጉስ፣ ኢየሱስ የቅድስና እና የጸጋ ንጉሥ፣ ኢየሱስ የሰላም፣ የፍትህ እና የፍቅር ንጉሥ ነው።

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንም ይሄንን ዘላለማዊ ንጉስ ለማክበር በየዓመቱ ታላቅ ዝግጅት በማድረግ የምታከብር ሲሆን፥ ዘንድሮም እንደወትሮው በዋዜማው ከተከናወኑ የወጣት ካቶሊካዊያን ዝግጅቶች ጀምሮ ህዳር 29 ቀን 2017 ዓ.ም. በልደታ ማሪያም ካቴድራል ከተለያዩ ቁምስናዎች የመጡ በርካታ ምዕመናን፣ ገዳማዊያት እና ገዳማዊያን በተገኙበት እና በብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነ ኢየሱስ ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካውያን በተመራ መስዋዕተ ቅዳሴ እና መንፈሳዊ አውደ ርዕይ በታላቅ ድምቀት ተከብሯል።    

 

 

 

 

09 December 2024, 14:50