አቡነ ደጀኔ፥ በሀገረ ስብከታቸው የምዕመናን ጥንካሬ የሚመነጨው "ሥር ከሰደደ እምነት ነው" አሉ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
በሶዶ ሀገረ ስብከት ውስጥ ምዕመናን ሥር የሰደደ ጠንካራ እምነት እንዳላቸው፣ በእግዚአብሔር የሚታመኑ እና መልካም ነገር እንደሚያደርግላቸው ተስፋ እንዳላቸው ገልጸዋል። የሶዶ ሐዋርያዊ ሰበካ ፍራንችስኮስዊ ጳጳስ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ደጀኔ ከ“ፊደስ” የዜና ማሰራጫ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፥ በተወለዱበት ሀገረ ስብከት ውስጥ ቅድሚያን ሰጥተው መሥራት የሚፈልጉት ሥራዎች የትኞቹ እንደሚሆኑ ገልጸዋል።
“በኢትዮጵያ የቅድስት መንበር እንደራሴ ተወካይ፥ ሀገረ ስብከቱን በጳጳስነት እንዳገልግል በጠየቁኝ ጊዜ የተሰማኝ ስሜት እጅግ ልዩ ነበር” ያሉት ብጹዕ አቡነ ደጀኔ፥ “ሃላፊነቱ ያልጠበቅሁት ቢሆንም እግዚአብሔር አገልግሎትን በዚህ መንገድ እንዳበረክት ስለ ፈለገ በምስጋና ተቀብየዋለሁ” ብለዋል።
የሀገረ ስብከቱ ጳጳስ ሆነው ከተመደቡ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በዱቦ ሉርድ እመቤታችን ማርያም ቁምስና እሑድ የካቲት 9/2017 ዓ. ም. የሚከበረውን ታላቅ ዓመታዊ በዓል በመስዋዕተ ቅዳሴ እንደሚያከብሩት ገልጸው፥ ከዚህ በፊት ከ1992 እስከ 1998 ዓ. ም. ድረስ ለስድስት ዓመታት ቁምስናውን በመሪነት ማገልገላቸውን አስታውሰዋል።
ከሹመታቸው ቀደም ብሎ በሰበካው የሐዋርያዊ አገልግሎት አስተባባሪ ሆነው ለሰባት ወራት እንደሠሩ ገልጸው፥ በእነዚያ ጊዜያት የሀገረ ስብከቱን እውነታ በሚገባ ለማወቅ መሞከራቸውን ተናግረዋል። በልዩ ልዩ ቁምስናዎች ውስጥ ቅድሚያ ሊሰጥባቸው የሚገቡ አገልግሎቶች የትኞቹ እንደሆኑ ለማወቅ በሰበካው ከሚገኙ ካኅናት፣ ገዳማውያን እና ገዳማዊያት ጋር መወያየታቸውን ተናግረው፥ ፍላጎቶቹ ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ እንደሆኑ እና በተለይ ወጣቶችን ጨምሮ ዕድሜያቸው ከ13 እስከ 14 ለሚሆናቸው አዳጊዎች የሚሰጥ የሐዋርያዊ አገልግሎት ጥማት ከፍተኛ እንደሆነ ለማወቅ መቻላቸውን አስረድተዋል።
ሀገረ ስብከታቸው በባሕላዊ ሆነ ፖለቲካዊ ይዘቱ ከፍተኛ ቁርጠኝነትን የሚጠይቅ ሰፊ ሀገረ ስብከት መሆኑን የገለጹት ብጹዕ አቡነ ደጀኔ፥ በደቡብ ከኬንያ፣ በደቡብ ምዕራብ ከጂማ ቦንጋ ሐዋርያዊ ሰበካ ጋር እንደሚዋሰን ተናግረው፥ ነገር ግን የተለያዩ ቋንቋዎች በሚነገሩበት እና ባሕሎች ባሉበት ሰፊ የሶዶ ሀገረ ስብከት ውስጥ ከገዳማዊያን እና ገዳማዊያት ጋር በመተጋገዝ ሐዋርያዊ አገልግሎት በማበርከት ላይ የሚገኙ የሀገረ ስብከት ካኅናት ሃያ አምስት ብቻ መሆናቸውን አስረድተዋል። አዳዲስ ተጨማሪ ቁምስናዎች እና የማኅበራዊ አገልግሎቶች እንዲኖሩ በመጠየቅ ላይ ለሚገኙ የአካባቢው ሕዝብ የካኅናት ቁጥር ማነሱ ትልቅ ተግዳሮት እንደሆነ ገልጸው፥ ይህን ለማቃለል ወጣቶችን ለማሰልጠን እንደሚያስቡ ገልጸዋል።
በብዙ ቁምስናዎች የካኅናት መኖሪያ ቤት የሌለ በመሆኑ ካኅናት ወደ ተለያዩ አካባቢዎች በየቀኑ ለመድረስ ከፍተኛ የገንዘብ ወጪ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል። “ቢሆንም ተስፋ አንቆርጥም!” ያሉት አቡነ ደጀኔ፥ በሀገረ ስብከቱ የሚገኙ ቁምስናዎች በወጣቶች የተሞሉ በመሆናቸው ከቁምስና መሪ ካኅናት፣ ከገዳማውያን እና ገዳማውያት ጋር በመተባበር ጥሪን ለማሳደግ በመጣር ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል።
“በአካባቢው ለካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የሚሰጣት ክብር እና ፍቅር ትልቅ ነው” ያሉት አቡነ ደጀኔ፥ በተለያዩ አካባቢዎች ለሚያከናውኗቸው ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች ከፍተኛ ምስጋና እንደሚቸርላቸው አስረድተዋል። “ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን በአገሪቱ ውስጥ ሰላምን ለማሰፍን የምታደርገው ጥረት ከፍተኛ በመሆኑ የመንግሥት ባለ ሥልጣናት ለሌሎች የሃይማኖት ተቋማት በሚሰጡት አክብሮት መጠን እንደሚያከብሯቸው ገልጸው፥ ቤተ ክርስቲያኒቱ ከሁሉም የሃይማኖት ተቋማት እና ማኅበረሰቦች ጋር አብሮ በሰላም የምትኖር በመሆኗ ትንሽ ግጭት በተፈጠረ ቁጥር ለማስታረቅ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያንን መጥራት እንደሚመርጡ አስረድተዋል።
"የትምህርት አገልግሎትን በተመለከተ ሁኔታው ከቦታ ቦታ የተለያየ ቢሆንም በአካባቢው ትምህርትን ለማሳደግ ያላቸውን ቁርጠኝነት እንደሚጠብቁ ገልጸው፥ ለምሳሌ በሶዶ ከተማ እና በአጠቃላይ ወላይታ ውስጥ ልጆችን ወደ ትምህርት ቤት መላክ አስፈላጊ ስለመሆኑ ያለው ግንዛቤ ዝቅተኛ የነበረ ቢሆንም ዛሬ ግን ሁሉም ሰው ልጆቹን ትምህርት ቤት ለማስገባት እንደሚፈልግ ገልጸዋል።
ከኬንያ ጋር በሚዋሰኑ የሀገረ ስብከቱ አካባቢዎች ሕጻናትን በተለይም ሴቶችን ትምህርት ቤት ማስገባት እንዳልተለመደ ገልጸው፥ በአንዳንድ አካባቢዎች ወጣቶች ዩኒቨርሲቲ እንደማገቡ እና የሥራ አጥ ቁጥርም ከፍተኛ በመሆኑ ለስደት እንደሚዳረጉ አስረድተዋል። ልጃገረዶች በአብዛኛው ወደ አረብ ሀገራት ተሰድደው ሃይማኖታቸውን እንደሚለውጡ፥ ወደ አውሮፓ ወይም ሌሎች አገራት የሚሰደዱትም በሚያሳዝን ሁኔታ ብዙውን ጊዜ በጉዞ ላይ በሚያጋጥማቸው አደጋ በባሕር ውስጥ ሞተው እንደሚቀሩ ገልጸዋል።
“ጠቅላላ የሕዝብ ቁጥሯ ወደ 120 ሚሊዮን እንደሚሆን በሚነገርባት ኢትዮጵያ ውስጥ ካቶሊካዊ ምዕመናን 2% ብቻ ቢሆንም በእምነት እና በተስፋ ሥር የሰደድን በመሆናችን ከሕዝብ ጋር ተባብረን መሥራታችንን እንቀጥላለን” ሲሉ በቅርቡ የሶዶ ሐዋርያዊ ሰበካ ጳጳስ ሆነው የተሾሙት ብጹዕ አቡነ ደጀኔ ሂዶቶ “ፊደስ” ከተሰኘ ካቶሊካዊ የዜና ማሰራጫ ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልስ ደምድመዋል።