ፈልግ

 እስራኤል ፍልስጤማውያን ራፋህን ለቀው እንዲወጡ ጠየቀች እስራኤል ፍልስጤማውያን ራፋህን ለቀው እንዲወጡ ጠየቀች  (AFP or licensors)

እስራኤል ፍልስጤማውያን ራፋህን ለቀው እንዲወጡ ጠየቀች

በቅድስት ሀገር እየተካሄደ ባለው ጦርነት ምክንያት እየደረሰ ያለው ስቃይ ቀጥሎ ባለበት በአሁኑ ወቅት የእስራኤል ጦር ፍልስጤማውያን የራፋን ክፍል ለቀው እንዲወጡ ጠይቋል።

አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የእስራኤል ጦር በደቡባዊ ጋዛ በምትገኘው ራፋህ ከተማ የሚኖሩ ሰዎች በከተማይቱ ላይ ሊሰነዘር ይችላል ተብሎ በሚጠበቀው ጥቃት ሰለባ ከመሆናቸው በፊት ቀደም ብሎ ወደተስፋፋው የሰብአዊ ቀጠና እንዲሄዱ አሳስቧል።

የእስራኤል መከላከለያ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ሌተናንት ኮሎኔል ናዳቭ ሾሻኒ እንዳሉት በራፋሕ የሚካሄደው ኦፕሬሽን “ውስን ስፋት ያለው” ነው ካሉ በኋላ፥ ቀነ ገደብ እንዳልተቀመጠና ነዋሪዎችን የማስወጣት ሂደት ቀስ በቀስ እንደሚካሄድ አክለዋል።  

የእስራኤል ጦር ማስጠንቀቂያ መስጠት የጀመረው በደቡባዊ ጋዛ ከሚያደርገው “የተወሰነ” ኦፕሬሽን በፊት እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፥ ወደ 100,000 ሺህ የሚጠጉ ፍልስጤማውያን እንዲሄዱበት የተጠየቁት ቦታ በካሀን ዩኑስ እና አል-ማዋሲ ከተሞች የሚገኙ ሰብአዊ መጠለያ ሥፍራ እንደሆነና ሆስፒታል፣ ምግብና መጠጥ እንዲሁም አስፈላጊ ነገሮች እንደሚገኙበት የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ገልጿል።  

የእስራኤል ጦር በምስራቃዊ ራፋህ ላይ ሊያደርግ ባቀደው ዘመቻ ንፁሀን ዜጎች ጥቃት እንዳይደርስባቸው አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ የሚጠይቅ በራሪ ወረቀቶች ለሊት ላይ እንደተበተኑ እንዲሁም በአጭር የጽሑፍ መልዕክት እና በማኅበራዊ ሚዲያ ማስጠንቀቂያ እየተሰጠ እንደሆነ ነው የተነገረው።

አንድ ከፍተኛ የሐማስ ባለሥልጣን እንዳስተወቁት እስራኤል ያወጣችውን ማስጠንቀቂያ “አደገኛ የነገሮች መጋጋል” ሲሉ ገልጸውታል።

የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር በራፋህ የሚገኘው ሐማስ ላይ ወታደራዊ እርምጃ መውሰድ እንደሚያስፈልግ ገልጸው፣ ነገር ግን እዚያ የተጠለሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሲቪሎች እጣ ፈንታ ላይ ሰፊ ዓለም አቀፍ ስጋት እንዳለ ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል እስራኤል በራፋህ ባደረገችው ጥቃት በአንድ ሌሊት ብቻ ቢያንስ 12 ሰዎች ሲገደሉ፣ በአጸፋው ሐማስ በከረም ሻሎም ማቋረጫ አቅራቢያ ባደረገው የሮኬት ጥቃት ሦስት የእስራኤል ወታደሮች መሞታቸው ተዘግቧል።

ይህ ሁሉ የተፈጸመው ምንም እንኳን ውይይቶቹ ውጤት ባያመጡም፥ አዲስ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ እና ታጋቾችን ለማስለቀቅ ተስፋ የተደረገበት ጥረት እየተደረገ ባለበት ወቅት ሲሆን፥ አሸማጋዮቹ አሁንም ጥረታቸውን መቀጠላቸው ተነግሯል።

በተባበሩት መንግሥታት የፍልስጤማውያን ስደተኞች ጉዳይ የሚከታተለው ክፍል ሊደርስ የሚችለው ጉዳት “ለ1.4 ሚሊዮን ሰዎች የከፋ ነው” ሲል አሳስቧል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሄዝቦላህ በእስራኤል ቁጥጥር ሥር በሚገኘው የጎላን ሃይትስ የእስራኤል የጦር ሰፈር ላይ በደርዘን የሚቆጠሩ ሮኬቶችን ማስወንጨፉን ተናግሯል። በኢራን የሚደገፈው ይህ ታጣቂ ቡድን የሮኬቱን ጥቃት የፈጸምኩት እስራኤል በሊባኖስ ላደረሰችው ጥቃት አጸፋዊ ምላሽ ነው ብሏል።

እስራኤል እስከ አሁን በወሰደችው ጥቃት ከ32,490 በላይ ሰዎች መገደላቸውን የጋዛ ጤና ሚኒስትር አስታውቋል።

 

08 May 2024, 09:50