ፈልግ

ህዳር 22 ቀን 2017 ዓ.ም. የሶሪያ መንግስት ባደረሰው የአየር ሃይል ጥቃት ተከትሎ ሰዎች በጥቃቱ የተጎዱ ሰፈሮችን እያዩ ህዳር 22 ቀን 2017 ዓ.ም. የሶሪያ መንግስት ባደረሰው የአየር ሃይል ጥቃት ተከትሎ ሰዎች በጥቃቱ የተጎዱ ሰፈሮችን እያዩ  (AFP or licensors)

በሶሪያ፣ አሌፖ ከተማ የሚገኘው የፍራንቺስካዊያን ‘ሆሊ ላንድ ኮሌጅ’ በቦምብ መመታቱ ተነገረ

በሶሪያ እየተካሄደ ያለው ግጭት እያገረሸ ባለበት በአሁኑ ወቅት፣ በአሌፖ የሚገኘው የፍራንቺስካዊያን ‘ሆሊ ላንድ ኮሌጅ’ በቦምብ ጥቃት ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰበት የተነገረ ሲሆን፥ የቅድስት ምድር ተንከባካቢ ካህን ስለሁኔታው ሲገልጹ “በሲቪሉ ማህበረሰብ መካከል ውጥረት እና ፍርሃት እየነገሰ መጥቷል” ብለዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በሶሪያ ሃገር፣ አሌፖ ከተማ የሚገኘው እና ፍራቺስካዊያን በባለቤትነት የሚያስተዳድሩት የሆሊ ላንድ ኮሌጅ ህዳር 22 ቀን 2017 ዓ.ም. በሩሲያ በተፈጸመ ጥቃት ክፉኛ ተጎድቷል።

ኮሌጁ የሚገኘው በገዳሙ የውስጠኛው ክፍል፣ ጥቃቱ በተፈጸመበት ምሽት መስዋዕተ ቅዳሴ እንዲደረግበት ታቅዶ በነበረበት ቤተክርስቲያን አጠገብ እንደሆነ ተመላክቷል።

'ከባድ ጉዳት ቢደርስም የሰው ህይወት አልጠፋም'
የቅድስት ሀገር ተንከባካቢ ካህን የሆኑት አባ ፍራንቸስኮ ፓቶን ጥቃቱን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ “በጥቃቱ ህንፃው ከፍተኛ ጉዳት ቢደርስበትም፣ እግዚአብሔር ይመስገን በሰው ላይ የደረሰ ምንም ዓይነት ጉዳት የለም” ያሉ ሲሆን፥ ሁሉም የገዳሙ አባቶች እና ምዕመናን በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ እና ከማህበሩ ጽ/ቤት ጋርም ጥሩ ግንኙነት እያደረጉ እንደሆነ ገልጸዋል።

ተንከባካቢ ካህኑ በማከልም የአከባቢው ህብረተሰብ በአሁኑ ወቅት ያለበትን ሁኔታ ሲገልጹ “በመካሄድ ላይ ባለው በማይገመተው ጦርነት ምክንያት በአሌፖ ከተማ በሚኖረው ሲቪሉ ማህበረሰብ ዘንድ ውጥረት እና ፍርሃት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መጥቷል” በማለት አብራርተዋል።

አባ ፓቶን በቅድስት ምድር ያሉ ክርስቲያኖች በሙሉ እና ሁሉም አብያተ ክርስቲያናት ለረጅም ዓመታት በጦርነት እና በዓመፅ ደቃ ለነበረችው ሶርያ ሰላም እንዲመጣ ጸሎት ለማድረግ በአንድነት እንዲሰባሰቡ አሳስበዋል። 

ከአስር ዓመታት በላይ ግጭት የነገሰባት ሶሪያ
ኮሌጁ ባለፉት አምስት ቀናት ውስጥ የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ በዓለም ላይ ካሉት ጥንታዊ ከተሞች አንዷ በሆነችው በአሌፖ በተካሄደ ጥቃት ከተጎዱት በርካታ ቦታዎች አንዱ ነው።

የሶሪያ የእርስ በርስ ጦርነት ከአስራ ሁለት ዓመታት በፊት የዴሞክራሲ ደጋፊ እና አቀንቃኝ በሆኑ ተቃዋሚዎች እና በመንግስት ኃይሎች መካከል በተፈጠረ ፖለቲካዊ ግጭት እንደተጀመረ ይታወሳል።

‘ጀብሃት አል ኑስራ’ ወይም ‘ኑስራ ፍሮንት’ በሚል ስያሜው የሚታወቀው አማጺ ቡድን በ2004 ዓ.ም. በሶሪያ ጦር የተነጠቀውን አሌፖ ከተማን ዳግም መቆጣጠሩን የሚያሳዩ ምስሎች እየወጡ ሲሆን፥ የሰብአዊ መብቶች የታዛቢዎች ቡድንም ይሄንን አረጋግጧል።

በኢራን እና ሩሲያ የሚደገፈው እና በፕሬዚዳንት በሽር አል አሳድ የሚመራው የሶሪያ መንግስት ጦርም ለመልሶ ማጥቃት በሚገባ ለመደራጀት በሚል ከከተማዋ ለቆ መውጣቱን አሳውቋል።

የሶሪያ መንግስት የዜና ወኪል የሆነው ሳና እንደዘገበው ህዳር 22 ቀን 2017 ዓ.ም. የሶሪያ እና የሩሲያ አየር ሃይሎች በጋራ ከአሌፖ ወጣ ብሎ በሚገኝ ከተማ የአየር ድብደባ መፈጸማቸውን አረጋግጠዋል።

በተስፋ መቆየት
ግጭቱ ከተቀሰቀሰበት ህዳር 18 ጀምሮ ከ300 በላይ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፥ በትንሹ 15,000 ሰዎች ከመኖሪያ ቤታቸው መፈናቀላቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዘገባዎች ያመለክታሉ።

የሶሪያ አማፂ ሃይሎች ሃማ ክልልን በመቆጣጠራቸው እነዚህ አሃዞች ሊጨምሩ ይችላል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፥ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከአሌፖ ወደ ደማስቆ መግባቱም ተገልጿል።

አንዳንድ የአሌፖ ነዋሪዎች የማህበራዊ ሚዲያ መተግበሪያ በሆነው በዋትስአፕ እንደገለጹት ምንም እንኳን ተስፋቸው የተሟጠጠ ባይሆንም፥ “ከእንግዲህ በኋላ በዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆነው መቀጠል እንደማይችሉ” በመጥቀስ፥ በቦምብ ፍንዳታ፣ በሰዓት እላፊ፣ በሞርታር እሳት እና በአነጣጥሮ ተኳሾች መካከል መኖር የዕለት ተዕለት ኑሮን ከባድ እንደሚያደርገው ገልጸዋል።
 

03 December 2024, 14:19