ፈልግ

መጠልያ ፍለጋ ወደ ቻድ እየተሰደዱ የሚገኙ ሱዳናውያን - የማህደር ምስል  መጠልያ ፍለጋ ወደ ቻድ እየተሰደዱ የሚገኙ ሱዳናውያን - የማህደር ምስል   (ZOHRA BENSEMRA)

እየተካሄደ ባለው የሱዳን ጦርነት ተጠናክሮ በቀጠለው ጥቃት በርካታ ንፁሀን ዜጎች እየሞቱ እንደሚገኝ ተገለጸ

በሱዳን ምዕራብ ዳርፉር ግዛት ውስጥ በሚገኝ የገበያ ቦታ በደረሰ የአየር ጥቃት አብዛኛዎቹ ሰላማዊ ሰዎች የሆኑበት ቢያንስ 100 ሰዎች መሞታቸው የተነገረ ሲሆን፥ ጥቃቱንም ያደረሰው የሱዳን ጦር በወሰደው የአየር ጥቃት ነው በሚል እየተከሰሰ ይገኛል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በሰሜን ዳርፉር በምትገኘው የካብካቢያ ከተማ ውስጥ በሚገኝ የገበያ ሥፍራ በተጣሉ ከስምንት በላይ ቦምቦች ከ100 በላይ ንፁሀን ዜጎች ሲሞቱ በርካቶች ቆስለዋል።

ህዳር 30 ቀን 2017 ዓ.ም. ሰኞ ዕለት በሳምንታዊው የገበያ ሥፍራ መፈጸሙ የተነገረለት አስከፊ እልቂትን ያስከተለው ጥቃት ዓለም አቀፍ ህግጋቶችን በግልፅ የጣሰ እንደሆነ የተነገረ ሲሆን፥ ይህ ጥቃት የተከሰተውም በሀገሪቱ እየተካሄደ ባለው በዓለም ላይ እጅግ አስከፊ የሆነ የሰብአዊ ቀውስን ያስከተለው የሱዳን ጦር ከፈጣን ድጋፍ ሰጭ ሃይሎች ጋር እያካሄዱት ባለው ከፍተኛ የእርስ በርስ እልቂትን ባስከተለው ጦርነት ምክንያት እንደሆነ ተገልጿል።

በጀኔራል አብደል ፋታህ አል ቡርሃን በሚመራው የሱዳኑ ጦር እና በመሀመድ ሃምዳን ዳጋሎ (ሄሜቲ) በሚመራው የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ጦር (አር.ኤስ.ኤፍ.) መካከል የተከሰተው 20 ወራትን ያስቆጠረው እና የዓለም አቀፉን ትኩረት ያጣው ጦርነት ወደ ከፍተኛ ደም አፋሳሽነት እየተቀየረ በመምጣቱ በርካታ ሰዎች ህይወታቸውን እያጡበት ሲሆን፥ ባለፈው ሰኞ እና ማክሰኞ ዕለት በተፈጸመ ጥቃት እንኳን ቢያንስ 127 ሰዎች መሞታቸው ተገልጿል።

እ.አ.አ. መጋቢት 2023 የጀመረው እና የተኩስ አቁም ስምምነት ጥረቶችም የተቋረጡበት የሱዳን ጦርነት ወደ 10 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎችን ከቤት ንብረታቸው ማፈናቀሉን፣ በሃገሪቷ ረሀብን በከፍተኛ ደረጃ ማስፋፋቱን፥ እንዲሁም በአብዛኛው የፈጥኖ ደራሹ ጦር ተጠያቂ ነው የሚባልበትን ብሄር ተኮር የሆኑ ጥቃቶች ተፈጽመውበታል።

የፈጥኖ ደራሽ ጦር በሚቆጣጠረው የሀገሪቱ ግማሽ ያህል ክፍል ላይ ጦር ሰራዊቱ እየወሰደ ያለው የአየር ጥቃት እየጨመረ መምጣቱ የተነገረ ሲሆን፥ በአንፃሩ የፈጥኖ ደራሽ ሰራዊቱ ደግሞ በበርካታ መንደሮች ላይ ወረራ እና ከፍተኛ የመድፍ ጥቃቶችን እያደረሰ እንደሆነ እና ሁለቱም ሃይላት ጥቃቱን የሚያነጣጥሩት ሲቪል ነዋሪዎች በብዛት በሚኖሩበት አካባቢዎች ላይ እንደሆነ ዘገባዎች ያሳያሉ።

የሱዳን ጦር የግዛቱ ዋና ከተማ የሆነችውን አል ፋሺርን ለመቆጣጠር ከፈጣን ድጋፍ ሰጪ ሃይል ጋር በሚያደርገው ጦርነት በሰሜን ዳርፉር የሚገኙ ከተሞችን በተደጋጋሚ የአየር ድብደባ የሚያደርስባቸው ሲሆን፥ በዚህም ምክንያት ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች እና የበጎ አድራጎት ድርጅቶች በዳርፉር የዘር ማፅዳት እና መጠነ ሰፊ የጦር ወንጀሎች መፈጸማቸውን በማውገዝ፥ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዝምታን በመረጠበት በአሁኑ ወቅት አሁንም ሌላ የዘር ማጥፋት ሊካሄድ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።

የሱዳን ወታደራዊ ሃይሎች ፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ ለወታደራዊ አገልግሎት የሚጠቀምበትን ማንኛውንም ቦታ ኢላማ የማድረግ መብት እንዳለው በመግለጽ፥ ሆኖም ግን በካብካቢያ ላይ ለደረሰው ጥቃት ሃላፊነቱን እንደማይወስድ የገለጸ ሲሆን፥ የፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ በበኩሉ ጥቃቱን አስመልክቶ አስተያየት እንዲሰጥ ለቀረበለት ጥያቄ ወዲያውኑ ምላሽ አልሰጠም።

የቅርብ ጊዜ ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት በግጭቱ 60,000 ሰዎች መሞታቸውን እና ከ30 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ሰብአዊ ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ብሎም 12 ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ ከቤት ንብረታቸው እንደተፈናቀሉ እና በበርካታ አከባቢዎች ከፍተኛ ረሃብ መከሰቱን ይገልፃሉ።
 

12 December 2024, 13:14