ሁለት ወጣት ፍልስጤማዊያን ሴቶች ከ ‘አስተዳደራዊ እስራት’ መለቀቃቸው ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
አስተዳደራዊ እስራት አብዛኛውን ጊዜ ለደህንነት ሲባል አንድን ሰው ያለ ፍርድ የማሰር እና በቁጥጥር ሥር የማቆየት ተግባር ሲሆን፥ ዓላማውም ከቅጣት ይልቅ ቀድሞ የመከላከያ እርምጃ ላይ እንደሚያተኩር እና ብዙውን ጊዜ ተጠርጣሪው ለወደፊቱ ስጋት ሊሆን ይችላል በሚለው ሀሳብ ላይ የተመሰረተ ነው።
ሊያን ናስር እና ሊያን ካይድ የተባሉ ሁለት ፍልስጤማዊያን ወጣት ሴቶች ለስምንት ወራት ከታሰሩበት የእስራኤል “አስተዳደራዊ እስራት” የተፈቱት ባለፈው ህዳር 26 ቀን 2017 ዓ.ም. ሲሆን፥ የሴቶቹ የመፈታት ዜና መጀመሪያ ላይ የተሰራጨው የማህበራዊ ሚዲያ መተግበሪያ በሆነው በቴሌግራም በኩል እንደሆነ፥ በኋላም በቅድስት መንበር የፍልስጤም አምባሳደር የሆኑት ኢሳ ካሲሴህ የዜናውን ትክክለኛነት ማረጋገጣቸው ተነግሯል።
አምባሳደሩ ለቫቲካን ዜና አገልግሎት በስልክ በሰጡት መግለጫ “በዚህ ጉዳይ ላይ የሠሩትን እና ሁለቱን ወጣት ሴቶች ነፃ ለማውጣት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ያበረከቱትን ሁሉ ማመስገን እፈልጋለሁ” ሲሉ አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
ከዚህን ቀደም ሚያዚያ ወር ላይ ‘ላ ኦዘርቫቶሬ ሮማኖ’ የተባለው የቫቲካን ዕለታዊ ጋዜጣ የሊያንን ጉዳይ እንዲሁም ስለ አወዛጋቢው “አስተዳደራዊ እስር” ጉዳይ በእትሙ አውጥቶ እንደነበር ይታወሳል።
ይህ እርምጃ ባለስልጣናት ግለሰቦችን ያለ ምንም ክስ ወይም ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ከደህንነት ጋር በተያያዙ ጥርጣሬዎች ላይ ተመስርቶ ለታሳሪውም ሆነ ለህግ አማካሪው ሳይገለጽ እንዲያስሩ ያስችላቸዋል።
እስሩ እስከ ስድስት ወር ድረስ የሚቆይ እና ብዙ ጊዜ ሊራዘም የሚችል ሲሆን፥ ከጥቂት ቀናት በፊት የእስራኤል አዲሱ የመከላከያ ሚኒስትር እስራኤል ካትስ ከአሁን በኋላ በፍልስጤም ግዛቶች ውስጥ በሚገኙ እስራኤላዊያን ሰፋሪዎች ላይ አስተዳደራዊ እስራት ተግባራዊ እንደማይሆን፣ ነገር ግን በፍልስጤማዊያን ዜጎች ላይ ህጉ እንደሚቀጥል ማሳወቃቸውን ተከትሎ ውዝግብ አስነስቶ እንደነበር ይታወሳል።
ባለፈው ወር በኢየሩሳሌም የሚገኘው የቫቲካን ዜና ባልደረባ የሊያን እናት ከሆኑት ወይዘሮ ሉሉ አራንኪ ናስር ጋር ቃለ ምልልስ አድርጎ የነበረ ሲሆን፥ ቃለ ምልልሱም ህዳር 3 ቀን 2017 ዓ.ም. ለንባብ በወጣው የ ‘ላ ኦዘርቫቶሬ ሮማኖ’ ጋዜጣ ላይ ወጥቶ ነበር።
በቃለ ምልልሱ ወቅት የሊያን እናት ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ድጋፍና ጸሎታቸው እንዳይለያቸው ደብዳቤ ጽፈውላቸው እንደነበር የገለጹ ሲሆን፥ ሴት ልጃቸው በእስር ላይ በቆየችባቸው ወራት ሁሉ እንዲጎበኟት ፍቃድ ተሰጥቷቸው እንደማያውቅም ጭምር ተናግረዋል።
ከዚህም ባለፈ የሃገረ ስብከቱ ካህን ቅዱስ ቁርባንን ለሊያን ናሳር ለማድረስ ሞክረው እንደተከለከሉ ተገልጿል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ባለፈው ሐሙስ ምሽት የሁለቱ ወጣት ሴቶች መከራ ማብቃቱ የተገለጸ ሲሆን፥ ሆኖም ግን አሁንም ድረስ ወደ 10,000 የሚጠጉ ፍልስጤማውያን በተመሳሳይ ሁኔታ እጣ ፈንታቸውን እየተጠባበቁ እንደሚገኝ ተነግሯል።