ኢየሱስ የዓለም ንጉሥ ኢየሱስ የዓለም ንጉሥ  (©paracchini - stock.adobe.com)

የኅዳር 29/2017 ዓ.ም የ34ኛው እለተ ሰንበት ንባባት እና የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ!

የእለቱ ንባባት

1.    ት. ዳንኤል 7፡13-14

2.    መዝሙር 92

3.    ራዕይ 1፡5-8

4.    ዮሐ. 18፡33-37

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

ጲላጦስም እንደ ገና ወደ ገዡ ግቢ ገባና ኢየሱስን ጠርቶ የአይሁድ ንጉሥ አንተ ነህን? አለው። ኢየሱስም መልሶ አንተ ይህን የምትለው ከራስህ ነውን ወይስ ሌሎች ስለ እኔ ነገሩህን? አለው። ጲላጦስ መልሶ እኔ አይሁዳዊ ነኝን? ወገኖችህና የካህናት አለቆች ለእኔ አሳልፈው ሰጡህ፤ ምን አድርገሃል? አለው።
ኢየሱስም መልሶ መንግሥቴ ከዚህ ዓለም አይደለችም፤ መንግሥቴስ ከዚህ ዓለም ብትሆን፥ ወደ አይሁድ እንዳልሰጥ ሎሌዎቼ ይዋጉልኝ ነበር፤ አሁን ግን መንግሥቴ ከዚህ አይደለችም አለው። ጲላጦስም እንግዲያ ንጉሥ ነህን? አለው። ኢየሱስም መልሶ "እኔ ንጉሥ እንደ ሆንሁ አንተ ትላለህ። እኔ ለእውነት ልመሰክር ስለዚህ ተወልጃለሁ ስለዚህም ወደ ዓለም መጥቻለሁ፤ ከእውነት የሆነ ሁሉ ድምፄን ይሰማል" አለው።

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ

በዓመቱ የስርዓተ አምልኮ ማብቂያ ላይ የምናከብረው “ክርስቶስ የዓለም ንጉሥ” ዓመታዊ በዓል የፍጥረታት ሕይወት እንዲሁ በአጋጣሚ የተገኘ ነገር እንዳልሆነ፣ ነገር ግን ወደ አንድ መጨረሻ ግብ የሚያመራ፡ የታሪኮች እና የፍጥረታት ሁሉ ጌታ ወደ ሆነው ወደ ክርስቶስ የመጨረሻ ግልጸት እንደ ሚያመራ የሚያሳይ ነው። የታሪኩ መደምደሚያ ዘለዓለማዊ መንግሥቱ ይሆናል ማለት ነው። በዮሐንስ 18፡33-37 ላይ ስለ ክርስቶስ መንግሥት፣ ስለ ኢየሱስ መንግሥት፣ ኢየሱስ በጌተሰማኒ ከታሰረ በኋላ ስለደረሰበት የውርደት ሁኔታ በመጥቀስ ያሳለፈውን ታሪክ ያመለክታል፡ "ታስሯል፣ ተሰድቡዋል፣ ተከሱዋል በኢየሩሳሌም ባለሥልጣናት ፊት ቀርቦአል"። ከዚያም በኋላ ፖለቲካዊ ለሆነ ሥልጣን እና የአይሁድ ንጉሥ ለመሆን እንደ ሚፈልግ ተደርጎ በሮም አቃቤ ሕግ ፊት እንዲቆም ይደረጋል። ጲላጦስ ጥያቄውን በማቅረብ አስገራሚ የሆነ ምርመራ ማድረግ በጀመረበት ወቅት እርሱ ንጉሥ መሆን አለመሆኑን ለማረጋገጥ ሁለት ጊዜ ይጠይቀዋል (ዮሐ 18፡33፣37)።

ኢየሱስም በቅድሚያ “የእኔ ምንግሥት ከዚህ ዓለም አይደለችም” በማለት ይመልሳል። ከዚያን በኋላ ደግሞ “አንተ እንዳልከው ነኝ” በማለት ያረጋግጣል። ይህም ኢየሱስ በመላው ሕይወቱ ፖለቲካዊ ለሆነ ስልጣን ምንም ዓይነት ፍላጎት እንዳልነበረው ያሳያል።

ኢየሱስ በአምስት እንጀራ እና በሁለት ዓሳ ብቻ 5ሺ የሚሆኑ ሰዎችን ከመገበ በኃላ በዚህ ተዓምር እጅግ በጣም ተደንቀው የነበሩ ሰዎች የሮማን መንግሥት ገርስሶ የእስራኤል መንግሥት እንዲገነባ ፈልገው እርሱን ልያነግሱት ፈልገው እንደ ነበረ እናስታውሳለን። ነገር ግን ለኢየሱስ መንግሥት ማለት ርዕዮት፣ ብጥብጥ እና መሳሪያ የታጠቀ ኃይል ማለት አይደለም። 5ሺ ሰዎችን በአምስት እንጀራ እና በሁለት ዓሳ ከመገበ በኋላ ሕዝቡ ልያነግሡት በፈለጉ ወቅት እነርሱን ትቶ ወደ ተራራ የወጣው በዚሁ ምክንያት ነው (ዮሐ 6፡5-15)። አሁን ለጲላጦስ መልስ ሲሰጥ ደቀ መዛሙርቱ እሱን ለመከላከል አልተዋጉም ነበር። “መንግሥቴ ከዚህ ዓለም አይደለችም፤ መንግሥቴስ ከዚህ ዓለም ብትሆን፥ ወደ አይሁድ እንዳልሰጥ ሎሌዎቼ ይዋጉልኝ ነበር፤ አሁን ግን መንግሥቴ ከዚህ አይደለችም” (ዮሐ. 18፡36) በማለት የመለሰውም በዚሁ ምክንያት ነው። ኢየሱስ ከፖለቲካው ኃይል በላይ እጅግ የላቀ የሆነ፣ በሰው ልጆች አማካይነት ሥልጣን ላይ ያልተቀመጠ መሆኑን ግልፅ ማድረግ ይፈልጋል። እርሱ ወደ ምድር የመጣው ኃይል ተጠቅሞ ዓለምን ለመግዛት ሳይሆን በፍቅር ስለእውነት ለመመስከር ነው። ይህም የቅዱስ ወንጌል ዋና መልእክት የሆነው “እግዚኣብሔር ፍቅር ነው” የሚለው መለኮታዊ እውነት ሲሆን እርሱ በዓለም ውስጥ የእርሱን የፍቅር፣ የፍትህ እና የሰለም መንግሥት ለመመስረት ነው የመጣው። እናም ይህ ኢየሱስ የነገሠበት እና እስከ መጨረሻው ዘመን የሚዘልቅ ነው። ከታሪክ እንደ ምንማረው በጦር መሳሪያ እና በምድራዊ ስልጣን ላይ  መሰርቱን በማድረግ የተገነባ መንግሥት በመጀመሪያ በቀላሉ ይበታተናሉ ቀጥሎም ብዙ ሳይቆይ ተዳክመው የፈራርሳሉ። ነገር ግን የእግዚአብሔር መንግሥት በፍቅር ላይ የተመሰረተ እና በልባችን ውስጥ ሥር መሰረት ያለው ነው፡ የእግዚኣብሔር መንግሥት በልባችን ውስጥ ሥሩን ይዘረጋል-ይህንን የሚቀበል ሰው ደግሞ ሰላምን ያገኛል፣ ነጻነትን ይጎናጸፋል ምልኣት ያለው ሕይወት ይኖራል። ሁላችንም ሰላምን እንፈልጋለን፣ ሁላችንም ነጻነት እንፈልጋለን፣ ሁላችንም ምልኣት ያለው ሕይወት እንፈልጋለን። ታዲያ ይህንን እንዴት ማግኘት እንችላለን? የእግዚአብሔር ፍቅር፣ የእግዚአብሔር መንግሥት፣ የኢየሱስ ፍቅር በልባችሁ ውስጥ ሥር እንዲሰድ ብታደርጉ ሰላም ታገኛላችሁ፣ ነጻነት ይኖራችኋል እንዲሁም ደስተኛ የሆነ ሕይወት ትኖራላችሁ።

ዛሬ ኢየሱስ እርሱ የሕይወታችን ንጉሥ ይሆን ዘንድ እንድንፈቅድለት ይጠይቀናል። በቃሉ፣ በመላካም አብነቱ፣ በመስቀል ላይ ተሰውቶ እኛን ከሞት ያዳነን ይህ ንጉሳችን የደጉን ሳምራዊ መንገድ እንድንከተል በማመልከት በጥርጣሬ ለተሞላው ሕይወታችን አዲስ የሕይወት ሕልውና ብርሃን በመስጠት ከፍርሃት ነጻ ሆንን እና በእየእለቱ ከሚገጥሙን ፈተናዎች ተላቀን እንድንኖር ይረዳናል። ነገር ግን እኛ የኢየሱስ መንግሥት ከዚህ ዓለም እንዳልሆነ ማስታወስ ይኖርብናል። አንዳንድ ጊዜ በስህተቶቻችንን እና በኃጢአቶቻችንን እንድንፈትሽ ጊዜ በመስጠት፣ የዓለምን እና የዓለም ምንግሥታት አምክንዮ  እንዳንከተል በማድረግ ህይወታችን አዲስ ትርጉም እንዲኖራት ያደርጋል።

ኢየሱስ ንጉሣችን ነው

ኢየሱስ ንጉሣችን ነው። አይሁዳውያን ኢየሱስን በጲላጦስ ፊት ካቆሙት በኋላ «የአይሁድ ንጉሥ ነኝ” ይላል እያሉ ከሰሱት። ጲላጦስም «የአይሁድ ንጉሥ ነህን?” የሚል ጥያቄ ለኢየሱስ አቀረበለት። ኢየሱስም መልሶ «አንተ ይህንን የምትለው ከራስህ ነውን ወይስ ሌሎች ስለ እኔ ነገሩህ?” አለው። ቀጥሎም ኢየሱስ «መንግሥቴ ከዚህ ዓለም ብትሆን ወደ አይሁድ እንዳልሰጥ ሎሌዎች ይዋጉልኝ ነበር። አሁን ግን መንግሥቴ ከዚህ አይደለችም´ (ዩሐ. 18፣36) አለው። ጲላጦስም «ታዲያ ንጉሥ ነህን?” አለው። ኢየሱስም «እኔን ንጉሥ እንደ ሆንኩ አንተ ትላለህ” አለው።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሳይወለድ ከብዙ ዘመናት በፊት ነቢዩ ዳዊት «አንተ ንጉሤና አምላኬ ነህ” (መዝ. 44፣4) እያለ ይተነበይለትና ይለምነው ነበር። ካህኑ ዘካሪያስ ደግሞ «ለጽዮን ልጅ ኢየሩሳሌም ንጉሥሽ እየመጣ ነው በሏት´ (ዘካ. 9፡9)) እያለ ይናገር ነበር። ቅዱስ ገብርኤል እግዚእተነ ማርያምን ምስጢረ ሥጋዌን ሲያበስራት ሳለ «ጌታ እግዚአብሔር አምላክ የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤ በያዕቆብ ቤት ላይም ያነግሠዋል፤ መንግሥቱም መጨረሻ የለውም” (ሉቃ. 1፣34)።

አይሁዳውያን አንድ ትልቅ ተአምር ስላዩ የእስራኤል ንጉሥ ብለው ይጠሩት ነበር። ነጥቀው ንጉሥ እንዲያደርጉት ይፈለጉ ነበር (ዮሐ. 6፣15)። በሕማማቱ ጊዜ «የአይሁድ ንጉሥ ሆይ ሰላም ለአንተ ይሁን” በማለት እያላገጡ ይሰግዱለት ነበር። ከተሰቀለ በኋላ ደግሞ «የአይሁድ ንጉሥ ከሆንክ ከመስቀል ላይ ውረድ በአንተ እናምናለን” (ሉቃ. 23፣37) በማለት ያዋርዱት ነበር። የኢየሱስ የአይሁድ ንጉሥ ብቻ አይደለም የዓለም ሕዝብ ሁሉ ንጉሥ ነው። የሁሉም ሕዝብ ንጉሥ እና ፈጣሪ ሲሆን በመንግሥቱ እንደ ሌሎች የዓለም ነገሥታት ለጥቂት ዓመታት አይደለም። የእርሱ መንግሥት ለዘለዓለም የሚኖር መጨረሻ የሌለው መንግሥት ነው (ሉቃ. 1፣33)። «ከባሕር እስከ ባሕር ሊገዛ፣ የምድር ነገሥታት ሁሉ ሊሰግዱለት፣ ሕዝቦችም ሁሉ እርሱን ሊያገለግሉ ነው” (መዝ. 71) ይላል ዳዊት። ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ «የነገሥታት ንጉሥ” በማለት ይጠራዋል (1ኛ. ጢሞ. 6፣15)።

ኢየሱስ ከፍጥረታት ሁሉ አስቀድሞ ንጉሥ ነው። ከኢምንትነት ወደ ሕይወት ወይም ወደ ዓለም አመጣን። እኛም የእርሱ ንብረትና ገንዘብ ነን። በሕይወት የሚያኖረን እርሱ ነው። በኋላ ደግሞ በማዳን በደኀንነት ዘመን እኛን ስለሚገዛን ዘለዓለማዊ ንጉሣችን ነው። በኃጢአት ወድቀን የሰይጣን ባርያዎች ስንሆን ከሰማይ ወደ ምድር ሊያድነን መጣ፤ ደሙንም አፍስሶ ተቤዠን፣ ከአስከፊ የሰይጣን ግዛት ነፃ አውጥቶን ወደ እርሱ ዘለዓለማዊ የደስታ ግዛት መለሰን፤ የመንግሥቱ ወራሾችም አደረገን።

ኢየሱስ በእርግጥ የነፍስና የሥጋ ንጉሥ ነው። በተለይ ደግሞ የነፈሳችን ንጉሥ ነው። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 11ኛ ለሕዝበ ክርስቲያን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ንጉሥነት ሲናገሩ «ነፍሶቻችን አንድ ታላቅ የዋህ ንጉሥ አላቸው፤ ይህ ንጉሥ ሊያድነንና ሕይወት ሊሰጠን ስለ እኛ ሞቷል። በመካከላችን እንዲኖር በእንጀራና በወይን መልክ ምስጢረ ቁርባንን ሠራልን። ይህም ቢሆንም ብዙዎች የእርሱ ተቃራኒዎች ሆነው ተነሥተዋል ወደ ሥጋቸው ፍላጐት እና ወደ ሰይጣን ባርነት ተመልሰዋል” ብለው ነበር።  

አይሁዳውያን ኢየሱስን ንጉሣቸውና መድኃኒታቸውን በሕይወት ዘመኑ ይወዱትና ያከብሩት ነበር። በተጨማሪ በሆሳዕና ቀን ደግሞ «በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ የተባረከ ይሁን” እያሉ በታላቅ ደስታ እና ክብር የተቀበሉት ሁሉ በሕማማቱ ሳምንት ካዱት ሰደቡት ረገሙት፣ ክፉኛ አዋረዱት አሰቃይተውም በመስቀል ላይ ሰቀሉት። ጲላጦስ «ንጉሣችሁ እንዳደረገው ትፈልጋላችሁ? ወይስ በነፃ ልልቀቀው?” እያለ ሲጠይቃቸው «ስቀለው ስቀለው …. ከቄሳር በቀር ሌላ ንጉሥ የለንም” አሉ። እኛስ በእንደዚህ ዓይነት ክህደትና ጭካኔ አንገኝምን? በአፋችን ኢየሱስ ንጉሣችን እያልን በሥራችን ስናዋርደው እንገኛለን። በኃጢአታችን ስናሳዝነውና እርሱን አስወግደን ሰይጣንን እና ዓለምን በልባችን አናነግሥምን?

እንደዚህ የምናደርግ ከሆነ ቶሎ ብለን እንታረም። በበደላችን ተጸጽተን በእግሩ ሥር ተደፍተን ከጠላቶቹ ተባብረን ስላሰቃየነው «ማረን” እንበለው። በተለይም ከእንግዲህ ወዲህ እንደማንክደውና እንደማንበድለው ይልቁንም እንደ ተወዳጅ ንጉሣችን አድርገን ልናገለግለው ዝግጁ እንደሆንን እናሳውቀው። ኢያሱ ለእስራኤል ልጆች «እናንተ እንደ አባቶቻችሁ ክፉ ነገሥታት ጣዖትን ማገለገል የምትፈልጉ ናችሁን? ወይስ እውነተኛ ንጉሥ የሆነውን አምላካችንን?” ካላቸው በኋላ ሁሉም በአንድነት ከእርሱ በስተቀር ሌላ ንጉሥ የለንም፤ ሌላ ንጉሥም ማገልገል አንፈልግም” አሉ። እኛም እንደዚህ እንበል እናድርግም።

ኢየሱስን የሕይወታችን ንጉሥ አድርገን እድንቀበል እና የእርሱ መንግሥት እንዲሰፋ ለማድረግ እውነት ለሆነው ለእርሱ ፍቅር ምስክርነት በመስጠት መኖር እንችል ዘንድ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትርዳን።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ አባ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

 

 

 

07 December 2024, 15:35