ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ፤  ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ፤  

ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ፥ "አንተ እና ሚስትህ"

ኢየሱስ ስለ ጋብቻ ሲናገር፣ በሁለተኛው ምዕራፉ ላይ ስለ ባልና ሚስት ድንቅና ዘርዘር ያለ ሥዕል ወደሚያሳየው ወደ ሌላው የኦሪት ዘፍጥረት ገጽ ይመራናል። አንደኛ፣ ሰው በእንስሳትና በዙሪያው ባለው ዓለም ውስጥ የብቸኝነት ስሜቱን ሊያቃልልለት የሚችል “ለእርሱ የሚስማማ ረዳት” (ዘፍ. 2፡ 18፣ 20) እንደሚፈልግ እናያለን። ፍቅርን በተመለከተ፣ ጸጥታ ሁልጊዜ ከቃላት በላይ ነውና፣ የጥንቱ የዕብራውያን አባባል ጸጥ ባለ ውይይት ውስጥ ቀጥታ ፣ የፊት ለፊት፣ የዐይን ለዐይን ግንኙነት እንዲኖር ያሳስባል። ይህ ግንኙነት ፣ የእግዚአብሔርን ፍቅርና በመጽሐፍ ቅዱስ የጥበብ አነጋገር “የሰው ትልቁ ሀብት፣ ለእርሱ የሚስማማ ረዳትና ደጋፊ ዓምድ” የሆነውን “አንተነትን” (ሲራክ 36፡24) የሚገልጽ መልክ ያለው  ግንኙነት ነው። ወይም በመኀልየ መኀልይ ዘሰሎሞን “ውዴ የእኔ ነው፣ እኔም የእርሱ ነኝ፤… እኔ የውዴ ነኝ፣ ውዴም የእኔ ነው” (ማኅ. 2፡16፤ 6፡ 3) በማለት ፍቅርዋንና ራስዋን አሳልፋ መስጠትዋን ድንቅ በሆነ መዝሙር እንደምትገልጽ ሴት ነው። 

የሰውን ብቸኝነት የሚያስወግድ ይህ ግንኙነት ለአዲስ ልደትና ለቤተሰብ መሠረት ይሆናል። የጊዜና የቦታ ባለቤት የሆነው አዳም፣ ከሚስቱ ጋር በመሆን፣ አዲስ ቤተሰብ መሠረተ። ኢየሱስም ስለዚህ ጉዳይ ኦሪት ዘፍጥረትን ጠቅሶ ሲናገር፣- “ሰው ከሚስቱ ጋር ይጣበቃል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ” ይላል (ማቴ. 19፡5፤ ዘፍጥ. 2፡24)። በጥንቱ የዕብራውያን አነጋገር “ይጣመራል”፣ “ይተሳሰራል” የሚለው ቃል፣ ጥልቅ ኅብርን፣ አካላዊና ውስጣዊ ቅርበትን የሚገልጽ ከመሆኑ የተነሣ፣ “ነፍሴ አንተን የሙጥኝ ብላለች” (መዝ. 63፡ 8) የሚለውን በእኛና በእግዚአብሔር መካከል ያለውን ኅብረት ለማመልከት ያገለግላል። ስለዚህ፣ የጋብቻ ትስስር በጾታዊና ሥጋዊ ገጽታው ብቻ ሳይሆን፣ በፍቅር ራስን አሳልፎ በመስጠትም ይገለጣል። በሁለቱም አካላዊ፣ ልባዊና ሕይወታዊ አንድነት፣ በመጨረሻም በሁለቱም ወላጆች “ሥጋ” አካላዊም መንፈሳዊም ሥነ ባሕርይ በሚካፈለው ልጅ አማካይነት የሁለቱም “አንድ ሥጋ መሆን” የዚህ አንድነት ውጤት ነው። 

ልጆችህ እንደ ወይራ ተክል ናቸው

አሁን ደግሞ የመዝሙረኛውን መዝሙር እንውሰድ። ባልና ሚስት በማእድ ላይ በተቀመጡበት ሁኔታ፣ ልጆች በጎናቸው “እንደ ወይራ ተክል” ናቸው (መዝ. 128፡3)፤ ማለትም በኃይልና በንቃት የተሞሉ ናቸው። ወላጆች የቤተሰብ መሠረት ናቸው ከተባለ፣ ልጆች ደግሞ የቤተሰብ “ሕያው ድንጋዮች” ናቸው ማለት ይቻላል (1ኛ ጴጥ. 2፡5)። ከእግዚአብሔር ስም (ያሕዌ፣ “ጌታ”) ቀጥሎ በብሉይ ኪዳን ውስጥ ተደጋግሞ የተነሣው ቃል ‹‹ልጅ›› (ቤን፣ “ልጅ”) ሲሆን፣ እርሱ ደግሞ “መገንባት” (ባና) ከሚለው ግሥ ጋር የተያያዘ ነው።  ስለዚህ፣ መዝሙር 128 ስለ ሕጻናት ስጦታ ሲናገር፣ የቤትና የማኅበራዊ ሕይወት ከተሞች ግንባታን በምሳሌነት ይጠቀማል፡- “እግዚአብሔር ቤትን ካልሠራ፣ ሠራተኞች በከንቱ ይደክማሉ፤… እነሆ ልጆች የእግዚአብሔር ስጦታ ናቸው። የማኅፀንም ፍሬ ከቸርነቱ የሚገኝ ነው። በጦረኛ እጅ እንዳሉ ፍላጾች ናቸው። ኮረጆዎቹ በእነዚህ የተሞሉ፣ የተባረከ ሰው ነው። ከጠላቶቻቸው ጋር በአደባባይ በሚሟገቱበት ጊዜ አይዋረዱም” (መዝ. 127፡ 1፣ 3-5)። እነዚህ ምሳሌዎች የጥንቱን ኅብረተሰብ ባህል የሚያንጸባርቁ ሲሆኑ፣ የልጆች መገኘት ደግሞ በድኅነት ታሪክ ውስጥ፣ ከትውልድ እስከ ትውልድ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው  የቤተሰብ ቀጣይነት ምልክት ነው። 

እዚህ ላይ ደግሞ፣ ሌላውን የቤተሰብ ገጽታ ማየት እንችላለን። አዲስ ኪዳን “ስለ ቤተሰብ አብያተ ክርስቲያናት” (1ኛ ቆሮ. 16፡ 19፤ ሮሜ 16፡5፤ ቆላ. 4፡15፤ ፊልሞ 2) እንደሚናገር እናውቃለን። የቤተሰብ ሳሎን የቤተሰብ ቤተክርስቲያን፣ የመሥዋዕተ ቅዳሴ ድባብ፣ በማዕዱ ላይ ኢየሱስ የሚገኝበት ሥፍራ ወደ መሆን ሊለወጥ ይችላል። በዮሐንስ ራእይ ውስጥ ጌታ “እነሆ፣ በደጅ ቆሜ አንኳኳለሁ፤ ማንም ድምፄን ሰምቶ በሩን ቢከፍትልኝ ወደ እርሱ ገብቼ ከእርሱ ጋር እበላለሁ፣ እርሱም ከእኔ ጋር ይበላል” (ራእይ 3፡20) ሲል የተናገረውን ምሳሌ ከቶ ልንረሳ አንችልም። እዚህ ላይ በእግዚአብሔር መኖር፣ በጋራ ጸሎትና በበረከት ሁሉ የተሞላ ቤት እናያለን። ይህም፣ “እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው እንዲህ ይባረካል። እግዚአብሔር ከጽዮን ይባርክህ” (መዝ. 128፡ 4-5) የሚለው ከላይ የጠቀስነው የመዝሙር 128 ትርጉም ማጠቃለያ ነው። 

ቤተሰብ ልጆች በእምነት የሚያድጉበት ስፍራ መሆኑንም መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ይህንንም ከፋሲካ ክብረ በዓል ማብራሪያ ዘጸ. 12፡ 26-27፤ ዘዳ. 6፡ 20-25 በግልጽ መረዳት ይቻላል። እንዲሁም ከፋሲካ ማእድ ሥነ ሥርዓት ጋር በተያያዘው በአይሁድ የውይይት ወግ (ሃጋዳ) ውስጥም ይኸው በግልጽ ታይቷል። ከዳዊት መዝሙሮች አንዱ በቤተሰብ ስለሚታወጀው እምነት ሲገልጽ እንዲህ ይላል፡- “ይህም የሰማነውና ያወቅነው፣ አባቶቻችንም የነገሩን ነው። እኛም ከልጆቻቸው አንደብቀውም፤ የእግዚአብሔርን ምሥጋና፣ ኃይሉንና ያደረገውን ድንቅ ሥራ፣ ለሚቀጥለው ትውልድ እንናገራለን። ለያዕቆብ ሥርዓትን መሠረተ፤ በእስራኤልም ሕግን ደነገገ፤ ልጆቻቸውንም እንዲያስተምሩ አባቶቻችንን አዘዘ። ይህም የሚቀጥለው ትውልድ እንዲያውቅ፣ እነርሱም በተራቸው ለልጆቻቸው፣ ገና ለሚወለዱት እንዲነግሩ ነው” (መዝ. 78፡ 3-6)። ስለዚህ፣ ቤተሰብ ወላጆች ለልጆቻቸው ዋናና ቀዳሚ የእምነት አስተማሪዎች የሚሆኑበት ሥፍራ ነው። እነርሱም ይህን የተማሩትን “ሙያ” ከአንዱ ሰው ወደ ሌላው ያስተላልፉታል። “በሚመጡት ዘመናት ልጅህ ‘ይህ ምን ማለት ነው?’ ብሎ ቢጠይቅህ እንዲህ በለው…” (ዘፀ. 13፡14)። በመሆኑም የሚቀጥሉት ትውልዶች “ወጣት ወንዶችና ደናግል፣ አረጋውያንና ልጆች ያመስግኑት” (መዝ. 148፡ 12) እያሉ ጌታን ማመስገን ይችላሉ። 

የመጽሐፍ ቅዱስ ሊቃውንት እንደሚያስገነዝቡን፣ (ምሳሌ. 3፡ 11-12፤ 6፡ 20-22፤ 13፡ 1፤ 22፡ 15፤ 23፡13-14፤ 29፡17) ወላጆች ለዚህ የማስተማር ሥራ ከባድ ኃላፊነት አለባቸው። ልጆች በበኩላቸው፣ “አባትህንና እናትህን አክብር” (ዘጸ. 20፡ 12) የሚለውን ትእዛዝ ማክበርና መለማመድ ይኖርባቸዋል። እዚህ ላይ፣ “ማክበር” የሚለው ቃል የቤተሰብና ማኅበራዊ ግዴታዎች ማሟላትን ይመለከታል፤ እነዚህንም ግዴታዎች በሃይማኖታዊ ሰበብ አስብቦ ችላ ማለት አይገባም (ማር. 7፡ 11-13)። “አባቱን የሚያከብር ልጅ ኃጢአቱ ይሰረይለታል፤ እናቱንም የሚያከብር ልጅ ድልብ እንደሚያደልብ ነው” (ሲራክ 3፡ 3-4)። 

ልጆች የወላጆች የግል ንብረት ሳይሆኑ የሚመሩት የራሳቸው ሕይወት እንዳላቸው ወንጌል ያስገነዝበናል። ኢየሱስ ለምድራዊ ወላጆቹ በመታዘዝና ራሱን ለእነርሱ በማስገዛት ምሳሌ ሆኖናል (ሉቃ. 2፡ 51)። ከዚህ ሌላ፣ የልጆች የሕይወት ውሳኔና ክርስቲያናዊ ጥሪአቸው ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ሲባል ከወላጆች መለየትን ሊጠይቅ ይችላል (ንጽ. ማቴ. 10፡ 34- 37፤ ሉቃ. 9፡ 59-62)። ኢየሱስ ራሱ ፣ በአሥራ ሁለት ዓመት ዕድሜው፣ ከምድራዊ ቤተሰቡ ሌላ የሚፈጽመው ትልቅ ተልእኮ እንዳለው ለማርያምና ለዮሴፍ ተናገረ (ንጽ. ሉቃ. 2፡ 48-50)። በዚህ መንገድ፣ በቤተሰብ ውስጥ እንኳ ሌላ ጥልቅ ትስስር እንደሚያስፈልግ ያሳየናል፤ “እናቴና ወንድሞቼስ የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው የሚያደርጉት ናቸው” (ሉቃ.8፡ 21) ይለናል። በተመሳሳይ፣ ኢየሱስ ለልጆች ካለው ተቆርkሪነት የተነሣ፣ ሕፃናት በየዋህነታቸውና ስለ ሌሎች ባላቸው ግብታዊ አስተሳሰብ እንደ አስተማሪዎች መሆናቸውን ሲገልጽ፣ “እውነት እላችኋለሁ፣ ካልተለወጣችሁ፣ እንደ ሕፃናት ካልሆናችሁ ፈጽሞ ወደ መንግሥተ ሰማይ አትገቡም። ስለዚህ በመንግሥተ ሰማይ ከሁሉ የሚበልጥ እንደዚህ ሕፃን ራሱን ዝቅ የሚያደርግ ነው” (ማቴ. 18፡ 3-4) አለ። በአንጻሩ በመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ሕፃናት ምንም መብት እንደ ሌላቸው፣ እንዲያውም እንደ ቤተሰብ ንብረት ይቆጠሩ እንደነበር ልብ ይበሉ። 

ምንጭ፡ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ “ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ” በሚል ርዕሠ ለጳጳሳት፣ ለካህናትና ለዲያቆናት፣ ለመነኮሳት፣ ለክርስቲያን ባለ ትዳሮች እና ለምእመናን በሙሉ ያስተላለፉት የድኅረ ሲኖዶስ ሐዋርያዊ ምክር ከአንቀጽ 12-17 ላይ የተወሰደ። 

አዘጋጅ አባ ዳንኤል ኃይለ

21 December 2024, 18:12