የሶርያ ክርስቲያን ማኅበረሰቦችን ሰብዓዊ ዕርዳታ እየደረሳቸው መሆኑ ተገለጸ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
“ምንም እንኳን በቅርቡ በሀገሪቱ ውስጥ ሁከት ቢፈጠርም፥ በሶርያ የሚገኙ ክርስቲያን ማኅበረሰቦች ሰብዓዊ ዕርዳታን እና ሐዋርያዊ አገልግሎት ድጋፍን በማግኘት ላይ ናቸው” ሲሉ የክልሉ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሚሼል ኮንስታንቲን ገልጸዋል። ዋና ዳይሬክተሩ በታኅሳስ 1/2017 ዓ. ም. ሪፖርታቸው፥ የዕርዳታ ቡድናቸው ከቁምስና አጋሮቻቸው ጋር ተገናኝተው ሁኔታው የተረጋጋ መሆኑን አረጋግጠዋል። የበሽር አል አሳድ አገዛዝ ኅዳር 29/2017 ዓ. ም. በወደቀ ጊዜ በሶርያ ውስጥ ያለው የክርስቲያን ማኅበረሰብ የተለያዩ ስሜቶችን የገለጸ ቢሆንም፥ ሁኔታዎች ይሻላሉ የሚል ተስፋ ያለው መሆኑን አቶ ሚሼል ገልጸዋል።
የቤተ ክርስቲያን ባለስልጣናት አዲሱ አገዛዝ በአብዛኛዎቹ የሶርያ ትላልቅ ከተሞች ውስጥ ለሚኖሩ ማኅበረሰቦች በተለይም የክርስቲያኖችን ድኅንነት ለመጠበቅ ቁርጠኛ እንደሚሆን መናገራቸው ይታወሳል። ሦስቱም የሶርያ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርኮች በማከልም፥ “ዘራፊዎች እና ወንበዴዎች ከሁኔታው ተጠቃሚ እንዳይሆኑ ለማድረግ አሁን እየታዩ ያሉ የሁከት እና የብጥብጥ ድርጊቶች በሙሉ ቁጥጥር ይደረግባቸል” ተብሎ እንደተነገራቸው ገልጸዋል።
የአንጾኪያው ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ ዮሐንስ አሥረኛን ጨምሮ የሶርያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ ኤፍሬም ዳግማዊ እና የመልቃይት ግሪክ-ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ የሴፍ አብሲ፥ “አዲሱ አገዛዝ ጥረቶቹን በማስተባበር ከሕዝባቸው ጎን እንዲቆም” በማለት ጥሪያቸውን አቅርበው፥ “ክርስቲያናዊ ህልውናን በመጠበቅ የዜግነት እና አብሮ የመኖር እሴቶችን የማስከበር አስፈላጊነትን” አጉልተው መናገራቸውን “ዘታይምስ” የተሰኘ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ በታኅሣሥ 2/2017 ዓ. ም. ሪፖርቱ አስታውቋል።
አቶ ሚሼል “ከአሳድ መንግሥት ውድቀት በኋላ በሶርያ ያለው አዲስ ሁኔታ በሦስት ወገኖኖች መካከል የተፈጠረ የሚዛን መበላሸት” ሲሉ ገልጸውታል። እነዚህም ዋና ዋና ከተሞችን ጨምሮ 65 በመቶው የሚሆነውን የሶርያ ግዛት የተቆጣጠሩት አማፂያን፣ በሰሜን እና ምሥራቅ ክልሎች 30 በመቶ የሚሆነውን የሶርያ ግዛት የሚቆጣጠሩት ኩርዶች እና በደቡብ ድንበር አካባቢ የሚገኘውን የድሩዝ አናሳዎች ጎሳዎችን ሌላው አማፂ ቡድን እንደሚቆጣጠረው ታውቋል።
የእስላማዊው ታጣቂ ቡድን ሀያት ታህሪር አል ሻም (ኤች.ቲ.ኤስ.) የሶርያን የሽግግር መንግሥት እንዲመራ ታኅሳስ 1/2017 ዓ. ም. አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር መሐመድ አልበሽርን መሾሙ ታውቋል።“ከብሔራዊ ምክር ቤት ጋር ምክክር ሳይደረግ የተደረገው ሹመት በሶርያ የፖለቲካ ባለስልጣን ወታደራዊ ቁጥጥር ላይ የተመሠረተ የአዲስ አቅጣጫ ምልክት ሊሆን ይችላል” ያሉት አቶ ሚሼል፥ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ተጽዕኖን በመፍጠር እና ሰላማዊ ሽግግር እንዲደረግ ግፊት በማድረግ ረገድ ሊጫወት የሚችለው ሚና መኖሩን ገልጸዋል።
ታጣቂው ቡድን የአልቃይዳ ቅርንጫፍ እንደመሆኑ ከዚህ አሸባሪ ቡድን ጋር ያለውን ሃይማኖታዊ ግንኙነት እና የፖለቲካ መሠረትን ደብቆ እንደማያውቅ ገልጸው፥ "ይህ የፖለቲካ ሂደት ውሎ አድሮ በአንድ በኩል ሕገ መንግሥቱን በመቀየር አዲስ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት በመገንባት በሌላ በኩል የአናሳዎችን መብት ያስከብራል” ብለዋል። ዜጎች በሀገሪቱ ውስጥ ያለው ስልጣን "ከሁሉም የሶርያ ማኅበረሰብ የፖለቲካ፣ የሀገራዊ እና የሀይማኖት ቁርሾዎች" ጋር ይጋራ እንደሆነ ለማየት እየጠበቁ እንደሚገኙ ታውቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሶርያ ፓውንድ በአስደናቂ ሁኔታ ማሽቆልቆሉ ለችግር የተጋለጡ ሶርያውያንን የበለጠ ለድህነት መዳረጉ ተነግሯል። የቱርክ ሊሬ ወይም የአሜሪካ ዶላር ምንዛሪ ለውጥ የኑሮ ውድነት እንዲጨምር ማድረጉ ሲነገር፥ ቁጥሩ እየጨመረ ለመጣው የሶርያ ቤተሰቦች እንደ ምግብ እና መድኃኒት እና ሌሎች መገልገያዎች እንደሚያስፈልጓቸው ታውቋል።