የር. ሊ. ጳ. ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ፋውንዴሽን የነጻ ትምህርት ዕድል ከሰጣቸው መካከል የር. ሊ. ጳ. ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ፋውንዴሽን የነጻ ትምህርት ዕድል ከሰጣቸው መካከል   (foto don Paweł Rytel-Andrianik)

ለተማሪዎች የነጻ ትምህርት ዕድል የሚሰጥ ጳጳሳዊ ፋውንዴሽን የምሥረታውን 25ኛ ዓመት አከበረ

በሮም ትምህርታቸውን ለሚከታተሉ የዘርዓ ክኅነት ተማሪዎች፣ ገዳማውያን እና ገዳማውያት እንዲሁም ምዕመናን የነፃ ትምህርት ዕድል የሚሰጠው የቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ፋውንዴሽን የምሥረታውን ሃያ አምስተኛ ዓመት አክብሯል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በአሜሪካ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1988 የተቋቋመው ጳጳሳዊ ፋውንዴሽኑ በአፍሪካ ትምህርት ቤቶችን በመገንባት፣ በላቲን አሜሪካ የሕክምና አገልግሎት በመስጠት እና የነፃ ትምህርት ዕድልን በመሳሰሉት ዘርፎች እገዛ አድርጓል። የምሥረታውን 25ኛ ዓመት ሐሙስ ኅዳር 26/2017 ዓ. ም. ያከበረው ጳጳሳዊ ፋውንዴሽኑ እስከ ዛሬ ወደ 2,000 የሚጠጉ ዕድለኞችን በሮም ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ማስቻሉ ታውቋል።

የፋውንዴሽኑ ዓለም አቀፋዊ ተልዕኮ
ጳጳሳዊ ፋውንዴሽኑ በያዝነው የአውሮፓውያኑ 2024 ብቻ ከ60 በላይ አገራት ውስጥ 118 ፕሮጀክቶችን የደገፈ ሲሆን፥ ውጥኖቹም የንጹህ ውሃ አቅርቦት፣ የትምህርት ቤት ግንባታን እና የክፍሎች እድሳትን ጨምሮ ለተጠቃሚው ኅብረተሰብ አስፈላጊ የሆኑ ሌሎች አገልግሎቶች እንዲሟሉ ሲያደርግ ቆይቷል።

የፋውንዴሽኑ ሌላው ድጋፍ ለስብከተ ወንጌል አገልግሎት እገዛ የሚያደርጉ የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮችን መተርጎም፣ አብያተ ክርስቲያናትን፣ ገዳማትን እና ትምህርት ቤቶችን መልሶ ማቋቋም፣ የሕክምና ተቋማትን መገንባት ሲሆን፥ እያንዳንዱ ፕሮጀክት በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የተቀመጡ ቅድሚያ የሚሰጥባቸውን ዕቅዶች ተከትሎ እንደሚፈጸም ታውቋል።

ፋውንዴሽኑ ከተመሠረተበት ጊዜ ወዲህ ከ225 ሚሊዮን ዶላር በላይ በማውጣት በተልዕኮው መሠረት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በዓለም ዙሪያ ሊሠሩ የሚፈልጓቸውን ሐዋርያዊ እና የበጎ አድራጎት ሥራዎችን ሲደግፍ መቆየቱ ታውቋል። ሥራዎቹ ስኬታማ ሊሆኑ የቻሉት ፋውንዴሽኑ ለሚያንቀሳቅሷቸው ፕሮጄክቶች ስጦታዎቻቸውን በሚያበረክቱ የገንዘብ ለጋሾች አስተዋፅዖ እንደሆነ ታውቋል።

እ.አ.አ 1998 ወሳኝ ዓመት ነበር
እንደ ጎርጎሮሳውያኑ 1998 የቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ፋውንዴሽን የነጻ ትምህርት ዕድል ፕሮግራም መጀመሩን የሚያመላክት ትልቅ ምዕራፍ እንደ ነበር ይታወሳል። ተነሳሽነቱ የተገኘው በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እና በወቅቱ ሊቀ መንበር በነበሩ በብፁዕ ካርዲናል ፍራንሲስ ኦኮነር መካከል በተደረገ ውይይት እንደ ነበር ታውቋል። ይህን ፕሮግራም ለመጀመር አቶ ጆን እና ወ/ሮ ካሮል ሴማን የተባሉት ለጋሾች የመጀመሪያውን የገንዘብ ድጋፍ ማድረጋቸው ታውቋል።

“ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ የነጻ ትምህርት ዕድል ፕሮግራም ያቀረቡት ጥያቄ ጥልቅ ግላዊ ነበር” ሲሉ ለቫቲካን የዜና አገልግሎት የተናገሩት ሚስተር ሲማን፥ የነጻ ትምህርት ዕድል በማግኘት ሮም በሚገኝ ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ከተማሩት መካከል ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ አንዱ እንደ ነበሩ አስታውሰው፥ ዕድሉ ለካኅናት፣ ለገዳማውያን እና ገዳማውያት እንዲሁም ለምዕመናን መሪዎችም እንዲሰጣቸው ሃሳብ ማቅረባቸውን ገልጸዋል።

በዚህም መሠረት ባለፉት 25 ዓመታት ውስጥ ለነጻ ትምህርት ዕድል መርሃ ግብር በተመደበ 16 ሚሊዮን ዶላር 1,959 ሰዎች በሮም ትምህርታቸውን መከታተል መቻላቸው ታውቋል።

ሕይወትን መለወጥ
የነጻ ትምህርት ዕድል አሸናፊዎች መካከል አንዷ የሆኑት ሕንዳዊ እህት ሐና ካፑናማይ በሮም የተከታተሉት ትምህርት ወጣቶች ማኅበራዊ ሚዲያን በአግባቡ እንዲጠቀሙ ለማሰልጠን እንደሚረዳቸው ተናግረዋል።

"ዛሬ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጽእኖ በወጣቶች እና ህፃናት ላይ እያደገ ነው" ያሉት እህት ሐና፥ ራዕያቸው ወጣቶች የግል እና ማኅበራዊ እሴቶቻቸውን በመጠበቅ ማንበብ እና መጻፍ የሚችሉ፣ ኃላፊነት የሚሰማቸው የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች እንዲሆኑ መርዳት እንደሆነ በመግለጽ ጳጳሳዊ ፋውንዴሽኑን፣ ሚስተር ጆን እና ሚስ ካሮል ሴማንን ለድጋፋቸው አመስግነዋል።

የኃላፊነት ጥሪ
የጳጳሳዊ ፋውንዴሽኑ የአስተዳደር ጉባኤ ሊቀ መንበር ብፁዕ ካርዲናል ሾን ኦማሌይ፥ በሉቃ. 12:48 ላይ “ብዙም ከተሰጠ ሰው ሁሉ ከእርሱ ብዙ ይፈለግበታል” የሚለውን በመጥቀስ፥ ድርጅታቸው ዓለም አቀፍ ኢ-ፍትሃዊነትን በመፍታት ረገድ የሚጫወተውን ሚና አፅንዖት ሰጥቷል።

ካርዲናል ኦማሌይ “በሃብታሞች እና በድሆች መካከል ያለው ልዩነት እያደገ ባለበት ማኅበረሰብ ውስጥ፣ የቅዱስ ጴጥሮስ የዕርዳታ ለጋሾች ለድሆች እና ለአደጋ ተጋላጭ ለሆኑ ሰዎች ቅድሚያ የመስጠት ሃላፊነታቸውን ይገነዘቡታል” ብለዋል።

የፋውንዴሽኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዴቪድ ሳቫጅም በማከል፥ “እነዚህ የገንዘብ ድጋፎች፣ የነጻ ትምህርት ዕድሎች እና የበጎ አድራጎት ሥራዎች ድርጅታችን ለካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የሚያበረክቷቸው ስጦታዎች ናቸው” ብለዋል።

ጳጳሳዊ እውቅና ያለው
ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር ላይ የጳጳሳዊ ፋውንዴሽን አባላት ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር በሮም መገናኘታቸው ይታወሳል። ቅዱስነታቸው ለአባላቱ ባደረጉት ንግግር፥ የተቸገሩትን ለመርዳት ጸሎት እና ስግደት የተነሳሽነት ምንጭ መሆናቸውን በማስገንዘብ፥ የፋውንዴሽኑ ወሳኝ ሚና በዓለም አቀፍ ደረጃ ትምህርታዊ፣ ሰብዓዊ እና ሐዋርያዊ ፕሮጀክቶችን በመደገፍ እንደሆነም ገልጸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ፋውንዴሽኑ በቤተ ክርስቲያኒቱ በኩል ለሚከናወኑ መንፈሳዊ እና ማኅበራዊ ሥራዎች ላደረጉት ዕርዳታ አድናቆታቸውን ገልጸው፥ ቀጣይነት ያለው ትብብር እና ሰላም እንዲሰፍን አሳስበው፥ የልግስናው ተካፋው እንደመሆናቸው፥ ጳሳዊ ፋውንዴሽኑ አንዳንድ አንገብጋቢ የዓለም ፈተናዎችን ለማሸነፍ እምነትን፣ ልግስናን እና ትብብርን ሃይሉ በማድረግ ምስክርነት እንደሚሰጥ ተናግረዋል።


 

07 December 2024, 15:44