በዩናይትድ ኪንግደም በእገዛ ራስን የማጥፋት ረቂቅ አዋጅ ከጸደቀ በኋላ የህጉ ተቃዋሚዎች ውሳኔውን በመቃወም ለጸሎት ተንበርክከው በዩናይትድ ኪንግደም በእገዛ ራስን የማጥፋት ረቂቅ አዋጅ ከጸደቀ በኋላ የህጉ ተቃዋሚዎች ውሳኔውን በመቃወም ለጸሎት ተንበርክከው   (AFP or licensors)

የዩናይትድ ኪንግደም ብጹአን ጳጳሳት የፓርላማ አባላት ‘በእገዛ ራስን የማጥፋት’ ህግን በመደገፋቸው ያላቸውን ቅሬታ ገለጹ

የእንግሊዝ እና የዌልስ የካቶሊክ ብጹአን ጳጳሳት የሃገሪቱ ፓርላማ አባላት አርብ ህዳር 21 ቀን 2017 ዓ.ም. ፈውስ በሌለው ህመም የሚሰቃዩ ህሙማንን በህክምና ድጋፍ ለማሳረፍ የሚያስችል አዲስ ረቂቅ አዋጅን ለማጽደቅ በሰጡት ድምጽ ከ 330 የሕግ አውጭዎች 275ቱ ረቂቅ አዋጁን በመደገፋቸው የተሰማቸውን ቅሬታ የገለጹ ሲሆን፥ ይህ አዲስ ረቂቅ ህግ ከስድስት ወር በታች በህይወት የመቆየት ዕድል ያላቸው በጽኑ የታመሙ ህሙማንን በሕክምና ዕርዳታ ለማሳረፍ መብት የሚሰጣቸውን አዲስ ህግን ብጹአን ጳጳሳቱ ከመጀመሪያው ጀምሮ ሲቃወሙት እንደነበር ይታወሳል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በሃገሪቱ ፓርላማ የተሰጠውን ድምጽ ተከትሎ፣ የህይወት ጉዳዮችን የሚከታተለውን ቢሮ የሚመሩት ብጹእ አቡነ ጆን ሸሪንግተን እንደተናገሩት፣ ህጉ በመርህ ደረጃ ጉድለት ያለበት እና አሳሳቢ የሆኑ አንቀፆችን የያዘ ነው ብለን እናምናለን ሲሉ ውጤቱ እንዳሳዘናቸው ገልጸዋል።

ብጹእ አቡነ ሼሪንግተን እንዳሉት የቀረበው ረቂቅ አዋጅ የአዕምሮ ብቃት ያላቸው እና ፈውስ በሌለው ሕመም የሚሰቃዩ ሰዎች በሁለት ዶክተሮች ፍቃድ እና በከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ ውሳኔ ሕይወታቸው እንዲያልፍ ማድረግን የሚያስችል በመሆኑ የካቶሊክ ብጹአን ጳጳሳት ህጉ ለህሙማን መብት ከለላ ስለማይሰጥ በእጅጉ እንደሚያሳስባቸው ገልጸው፥ በሕጉ ውስጥ የተካተቱት አንቀፆች ዶክተሮች የኅሊና መብትን በአግባቡ እንዳይተገብሩ የሚከለክሉ፣ በህክምና እርዳታ ህይወትን ማቋረጥ ተግባር ላይ ለመሳተፍ ለማይፈልጉ ሆስፒታሎች እና የእንክብካቤ ማዕከላት በቂ ጥበቃ የማይሰጥ እንደሆነ በመግለጽ ዶክተሮች ስለዚህ ጉዳይ ውይይት እንዲጀምሩ ያስችላቸዋል ብለዋል።

የህመም ማስታገሻ ህክምናን ጥራት እና አቅርቦትን በማሻሻል የህሙማኑን የመጨረሻ ስቃይን ለመቀነስ የሚያስችለውን ምርጡን መንገድ ችላ ያለ ህግ መሆኑን የጠቆሙት ጳጳሱ፥ የካቶሊክ ማህበረሰብ በፓርላማው ሂደት ላይ ያለው ይህ ህግ በመጨረሻ ውድቅ እንዲሆን ጸሎት እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

ይህ ባለፈው ዓርብ ዕለት የተደረገው ታሪካዊ ድምጽ ከሁለቱም ወገኖች የተውጣጡ የህግ አውጭዎች በውሳኔያቸው ላይ ትልቅ ተጽዕኖ የፈጠሩ የግል ታሪኮቻችውን ያካፈሉበትን ከአራት ሰዓታት በላይ የፈጀውን ስሜታዊ ክርክር ተከትሎ እንደነበር ተገልጿል።

የፓርላማ አባላቱ የፓርቲ መስመር ከመከተል ይልቅ በራሳቸው ኅሊና ላይ ተመርኩዘው ውሳኔ መስጠት የሚችሉበት ነፃ ድምፅ ተሰጥቷቸዋል።

ረቂቅ አዋጁ ሕሙማን፣ በተለይም አረጋውያን፣ አካል ጉዳተኞች ወይም አቅመ ደካሞች ሸክም እንዳይሆኑ በመስጋት ሕይወታቸውን እንዲያቋርጡ ጫና ሊያደርግባቸው እንደሚችል የሕጉ ተቃዋሚዎች ተናግረዋል። ከዚህም በተጨማሪ የካቶሊክ ሕክምና ማኅበር የቀረበው ሕግ ለሕመም ማስታገሻ እንክብካቤ እና ዶክተሮች ከታካሚው ጋር ላላቸው ግንኙነት አደገኛ እንደሚሆን ጠቁሞ፥ ይህም ለኅሊና ተቃውሞ ደካማ ጥበቃን እንደሚያደርግ እና በካቶሊክ የሚተዳደሩ እንክብካቤ መስጫ ተቋማት ሕጉን ሳይወዱ በግድ እንዲያከብሩት ሊገደዱ እንደሚችሉ ገልጿል። ከዚህም ባለፈ የብሪታንያ የሕክምና ማኅበር እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ2021 ጀምሮ በ ‘እገዛ ራስን ማጥፋት’ ላይ ገለልተኛ አቋም ይዞ ቆይቷል።

ብዙ የሕግ አውጭ አካላት ድምጽ ከመሰጠቱ በፊት ህጉን በደንብ ለመረዳት እና ለማገናዘብ በቂ ጊዜ ባለመኖሩ ያላቸውን ስጋት በመግለጽ፥ በሌሎች ሀገራት ያለው ህሙማን በህክምና እርዳታ እንዲያርፉ የሚደነግጉ ህጎች ብዙም ተቀባይነት እንደሌላቸው አንስተዋል።

በተለይም ለአደጋ ተጋላጭ ለሆኑ ሰዎች፣ አካል ጉዳተኞች እና በቂ ማኅበራዊ እንክብካቤ የሌላቸው አዛውንቶች ነፍሳቸው ያለ ጊዜ እንዲያልቅ ማድረግ የበደል እና የማስገደድ ጫና ሊሆንባቸው እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።

ረቂቅ አዋጁን የሚደግፉ ሰዎች በበኩላቸው ህጉ በህመም የሚሰቃዩ ሰዎች ምርጫ እንዲኖራቸው ያደርጋል በማለት ይከራከራሉ።

በድምጽ መስጫው ወቅት የካቶሊክ ብጹአን ጳጳሳት እና ሌሎች የሃይማኖት መሪዎች በሕጉ ሥነ ምግባራዊ እና ተግባራዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ስጋት ደጋግመው የገለጹ ሲሆን፥ የእንግሊዝ እና የዌልስ የካቶሊክ ብጹአን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት ብፁዕ ካርዲናል ቪንሰንት ኒኮልስ “የመሞት መብት በቀላሉ ወደ የመሞት ግዴታ ሊሸጋገር ይችላል” ሲሉ ደጋግመው አስጠንቅቀዋል።
 

02 December 2024, 09:51