ታህሳስ 10 ቀን 2017 ዓ.ም. የተከፈተው አዲሱ የቫቲካን ተንቀሳቃሽ ፖስታ ቤት ታህሳስ 10 ቀን 2017 ዓ.ም. የተከፈተው አዲሱ የቫቲካን ተንቀሳቃሽ ፖስታ ቤት   (AFP or licensors)

ቫቲካን አዲስ ፖስታ ቤት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ መክፈቷ ተነገረ

ቫቲካን ማንኛውም ሰው “የእግዚአብሔርን ቃል የያዙ መልዕክቶች መላክ እና መቀበል” የሚችልበት አዲስ ፖስታ ቤት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በደማቅ ስነ-ስርዓት ማስጀመሯ ተነግሯል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ታኅሣሥ 10 ቀን 2017 ዓ.ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በተካሄደ ደማቅ ሥነ ሥርዓት የተጀመረው ተንቀሳቃሽ ፖስታ ቤት ‘ፖስቴ ኢጣሊያኔ’ ተብሎ ከሚጠራው የጣሊያን የፖስታ አገልግሎት ድርጅት የተበረከተ መሆኑ የተነገረ ሲሆን፥ ቀድሞውንም ሥራ ላይ የነበረው ይህ ፖስታ ቤት ሃገሪቷን ለሚጎበኙ ለተለያዩ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና ጎብኚዎች ልዩ የፖስታ እና ቴምብር አገልግሎት እንዲሰጥ ተብሎ የተሰራ መሆኑ ተገልጿል።

በዝግጅቱ ላይ የቫቲካን ከተማ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር የሆኑት ብፁዕ ካርዲናል ቬርጌዝ አልዛጋ እና የጣሊያን ፖስታ ቤት አገልግሎት ዳይሬክተር ጁሴፔ ላስኮ እንዲሁም የግዛቱ ዋና ፀሐፊ ሲስተር ራፋኤላ ፔትሪኒ ተገኝተዋል።

አዲሱ የቫቲካን ተንቀሳቃሽ ፖስታ ቤት ከሌሎቹ ተቋማት ለየት የሚያደርገው መደበኛ ሥራ ወይም አገልግሎት ብቻ የሚሰጥበት ሳይሆን በእውነት “ሰዎች የእግዚአብሔርን የምስራቹን ቃል የሚላላኩበት፣ የሚቀበሉበት እና የሚገናኙበት” ልዩ እና እውነተኛ ቦታ መሆኑም ጭምር በሥነ ስርዓቱ ላይ ተገልጿል።

የመባረክ ሥነ ስርዓት
ፖስታ ቤቱ ተመርቆ ከተከፈተ በኋላ የቫቲካን ከተማ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ብጹዕ ካርዲናል ቬርጌዝ በቢሮው የተለያዩ ክፍሎች ላይ የተቀደሰ ውሃ የረጩ ሲሆን፥ በመቀጠልም ብጹዕነታቸው ከጣሊያን ፖስታ ቤት ዳይሬክተር ጋር በመሆን በህንፃው በስተግራ በኩል ባለው ግድግዳ ላይ ቅዱስ መስቀሉን ከሰቀሉ በኋላ ከጣሊያን ፖስታ ቤት መሰጠቱን በሚገልጸው የልገሳ ሰነድ ላይ ተፈራርመዋል።

የመገናኛ እና የትብብር አገልግሎት ቦታ
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ወቅት ብፁዕ ካርዲናል ቬርጌዝ አልዛጋ በወንጌል ውስጥ ስለተገለጸው የብስራት ቃል ላይ አስተንትኖ የሰጡ ሲሆን፥ ‘ከእግዚአብሔር የተላከውን የምስራቹን ቃል’ የሚያበስረው መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ‘እንደ ናዝሬት ያሉ እጅግ በጣም ትንሽ ወደሆኑት ቦታዎች’ እና ‘ማርያምን የመሳሰሉ ታናናሽ ሰዎች ጋር እንኳን የምስራቹን ቃል አድርሷል’ ሲሉ ተናግረዋል።

ብጹዕ ካርዲናሉ ሠራተኞችን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያንን፣ ጎብኝዎችን እና ማንኛውም ጽህፈት ቤቱን የሚጠቀም ሰውን ሁሉ ለእመቤታችን ቅድስት ማሪያም አደራ በመስጠት፣ ፖስታ ቤቱ “የመገናኛ እና የኅብረት አገልግሎት መስጫ ቦታ” ሆኖ እንደሚያገለግል ገልጸዋል።

ዘላቂ እና ተደራሽ የሆነ ቢሮ
በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በስተግራ በኩል የሚገኘው አዲሱ ጽሕፈት ቤት ሦስት የሥራ ቦታዎች ያሉት ሲሆን፥ እንጨትን ጨምሮ አነስተኛ የአካባቢ ብክለት ተጽዕኖ ባላቸው ነገሮች እንደተሠራ ተጠቁሟል።

ፖስታ ቤቱ ታህሳስ 11 ቀን 2003 ዓ.ም. የተቋቋመውን እና በያዝነው ዓመት ህዳር 26 ላይ አገልግሎት መስጠት ያቆመውን የቀድሞ ቢሮ በመተካት ሥራ እንደጀመረ የተገለጸ ሲሆን፥ መንፈሳዊ ነጋዲያንን፣ ጎብኝዎችን እና ሁሉንም ዜጎች ለመቀበል ዝግጁ የሆነው አዲሱ ቢሮ ከባህላዊ የፖስታ አገልግሎት በተጨማሪ ስለ ፖስታ ቴምብሮች እና የፖስታ አገልግሎት ታሪኮችን ለማጥናት የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎችንም እንደሚያቀርብ ተገልጿል።
 

23 December 2024, 14:16